የአፍ መሸፈኛ ጭምብል ማጥለቅ ከቫይረስ ይታደገን ይሆን?

ጭምብል የለበሱ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, KEVIN FRAYER

በቫይረስ የሚተላለፉ የትንፋሽ በሽታዎች ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የአፍ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎችን ፎቶ ማየት የተለመደ ነው።

የአፍ ጭንብሎች በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል ሁነኛ አማራጭ ናቸው፤ ታዋቂም ናቸው። ቻይናውያን በተለይ በነጯ ጭምብል ይታወቃሉ። ለበሽታ ብቻ ሳይሆን ለአየር ብክለት መከላከያም ጥቅም ላይ ይውላል።

የተላላፊ በሽታ ባለሙያዎች ግን የአፍ ጭንብሎቹ ይህን ያህል ጠቃሚ አይደሉም ይላሉ። ነገር ግን ጭምብሎቹ ከእጅ ወደ አፍ የሚተላለፍ በሽታን ለመከላከል ጠቃሚ እንደሆኑ የሚያስረዱ ጥናቶች አሉ።

በህክምናው አጠራር 'ሰርጂካል ማስክ' የሚል ስያሜ ያላቸው እኒህ ጭምበሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ነው። የስፔን ጉንፋን የሚል ስያሜ የተሰጠው ወረረሽኝ በፈረንጆቹ 1919 ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሲቀጥፍ ነው ጭንብሎቹ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት።

የሎንዶን ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ዴቪድ ካሪንግተን የአፍ ጭንብሎች አየር ላይ ያሉ ቫይረሶችንም ሆነ ባክቴሪያዎች ለመከላከል ሁነኛ አማራጭ ናቸው ብዬ አላስብም ይላሉ።

ምንም ጥቅም የላቸውም ማለት ግን አይደለም ይላሉ ዶክተሩ። ከእጅ ወደ አፍ የሚተላለፍ በሽታን ከማገድ አልፎ በማስነጠስ ወቅት ወይም በሳል የሚተላለፍ ቫይረስን ሊገቱ ይችላሉ ባይ ናቸው።

ጥናቶቹ አፍን በጭንብል ከማፈን በላይ በቫይረስ የሚተላለፉ የትንፋሽ በሽታዎችን ለመግታት እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና መታጠብ ሁነኛ መላ ነው ይላሉ። አልፎም ዓይንና አፍንጫን በእጅ አለመነካካት ይመከራል።

የአፍ ጭንብሎች በትክክል መደረግ አለባቸው፣ ቶሎ ቶሎ ሊቀየሩ ይገባል፣ በጥንቃቄ ማስወገደም ግድ ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስጠነቅቃሉ።

በቅርቡ በቻይና የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ሰዎች የአፍ ጭንብል እንዲያዘወትሩ ምክንያት ሆኗል።