ኢራን፤ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪውን በስቅላት ቀጥቻለሁ አለች

ኢራን፤ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን አባላትን በስቅላት ቀጣች

ኢራን፤ የገልፍ አዞ በመባል የሚታወቀውን አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡደን መሪ በስቅላት መቅጣቷን አሳወቀች።

በሃገሪቱ ቴሌቪዥን በተላለፈው ዘገባ ባለሥልጣናት፤ 'የአዞው' ቡድን አባላት ከ100 ቶን በላይ አደንዛዥ ዕፅ በውቅያኖስ ከሃገር ሃገር ሊያዘዋውሩ ሲሉ እንደተያዙ ተናግረዋል።

የ36 ዓመቱ መሪ እና አጋሩ ለዓመታት ምርመራ ከተካሄደበት በኋላ መገደሉን ባለሥልጣናቱ አሳውቀዋል።

ኢራን በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ እሥረኞችን በስቅላት ትቀጣለች።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የመብት ተሟጋች ቡደን አራን፤ በ2018 [በግሪጎሪ ኦቆጣጠር] ብቻ 253 ሰዎችን በስቅላት መቅጣቷን ያሳውቃል። 2017 ላይ ደግሞ 507 ሰዎች በስቅላት ተቀጥተዋል።

ምንም እንኳ ኢራን ፀረ-አደንዛዥ ዕፆች ላጥይ ታራምድ የነበረውን ጠበቅ ያለ ሕግ ብታላላም አሁንም ቢሆንም ዕፆቹን ይዞ ከሃገር ሃገር ለመዘዋወር መሞከር በሞት ያስቀጣል።

'አዞው' መልኩንና አድራሻውን በመቀያየር ሣራውን ሲከውን ነበር ሲሉ ዋና አቃቤ ሕግ አሊ ሳሌህ ለኢራኑ ኢስና የዜና ወኪል ተናግረዋል።

«በጣም ግዙፍና አደገኛ የሆነ ቡድን ነበር። ቡድኑ በኢራንና ጎረቤት ሃገራት ዕፅ ያዘዋውር ነበር።»

ኢራን የቡድኑን መሪ በስቅላት ከመቅጣት አልፋ ቡድኑ እንዳልነበር አድርጋ መበታተኗን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል። የቡድኑ አባላት ከዕፅ ዝውርር በሚያገኙት ገንዘብ 'ሪል ስቴት' ቢዝነስ ውስጥ ገብተው ቤት ሲቸበችቡ ነበር ያሉት አቃቤ ሕጉ ቤቶቹን መንግሥት ተረክቧቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።

የተቀሩት የቡድኑ አባላት ከአምስት ዓመት እሥር ጀምሮ ከባድ የሚባል የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ተነግሯል።

የኢራን ባለሥልጣናት፤ 'አዞው' የተባለው ግለሰብን ማንነት ግልፅ ለማድረግ አልሻቱም።