ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር በኋላ ሚዲያና የሚዲያ ቁጥጥር ምን ይመስላል?

ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን መለቀቃቸው፣ የግል መገናኛ ብዙሃን ቁጥር መጨመር ከታዩት ለውጦች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል።

በሌላ በኩል የሚዲያ አዘጋገቦች ከወገንተኝነት የፀዱ አለመሆናቸው ይህም በማኅበረሰብ መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት እንደሆኑ ተደጋግሞ ይነገራል።

ለዚህም ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ በሚዲያዎች ነፃ፣ ከወገንተኝነት የፀዳ፣ ሚዛናዊ እና ሙያዊ አዘጋገብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ቁጥጥር መላላት እንደሆነ ይጠቀሳል።

የድኅረ ዐብይ ሚዲያ በምሁራኑ ዕይታ

ብሮድካስት ባለሥልጣን ሥልጣኑ የት ድረስ ነው?

ዶ/ር ጌታቸው ድንቁ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

ዶ/ር ጌታቸው ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ለሚዲያ የተሻለች አገር እንድትሆን ብሮድካስት ባለሥልጣን የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራሉ።

"በሚዲያ ነፃነትና በሚዲያ ሙያ ጎረቤት አገር ኬንያ የተሻለች አገር ናት" የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው ከእነርሱ ልምድ ለመውሰድ የልዑካን ቡድኑን በመምራት እዚህ እኛ የምንገኝበት ኬንያ መጥተው ነበር።

በዚህ አጋጣሚም የቢቢሲን ቢሮ ለመጎብኘት ጎራ ባሉበት ወቅት፤ ከለውጡ በኋላ ያለውን የሚዲያ ዘገባ ይዘትና የቁጥጥር ሥራን አስመልክተን ቃለ ምልልስ አድርገንላቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚንትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአገሪቷ ያለውን የሚዲያ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?

ከፍተኛ መሻሻል አለ። ከብዝሃነት አንፃር ቁጥራቸው ጨምሯል። መንግሥት በፊት በተለይ ለኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ፈቃድ ለመስጠት ፈራ ተባ ይል ነበር። አሁን ግን ቁጥራቸው ጨምሯል። በተለይ በሳተላይት የሚሠራጩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለመጀመር የሚፈልጉ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ካቀረቡ ፈቃድ ይሰጣል።

ጋዜጦች [በቀጥታ እኛን ባይመለከቱም] ብዙ መፅሔቶችና ጋዜጦች ገበያ ላይ ይታያሉ። ተዘግተው የነበሩ ድረ ገፆችም ተከፍተው የተለያዩ መረጃዎች እያስተላለፉ፤ ሕብረተሰቡ መረጃ የሚያገኝባቸው አማራጮች በዝተዋል።

ነገር ግን አሁን በአንገብጋቢነት የሚነሳው የጥራት ችግርና ወገንተኝነት ነው። እንዲህ መሆኑም በብረተሰቡ ዘንድ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ ንደሆነ ይነገራል። ባለሥልጣኑ እዚህ ላይ ምን ይላል?

ታፍኖ የነበረ ሚዲያና የሚዲያ ምህዳር በሚከፈትበት ጊዜ ወደ ሜዳው መጥተው የሚጫወቱት ሁሉ ሙያዊ በሆነ መንገድ ሥራውን ይሠሩታል ተብሎ አይታሰብም። አንዳንዶች ነፃነቱን ተጠቅመው በኃላፊነት ሲሠሩ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለተለያየ ምክንያት ሚዲያውን ይጠቀሙበታል።

ለፖለቲካ አላማ ማስፈፀሚያ፣ ለቡድን ዓላማዎች ማስፈፀሚያ እንደሚጠቀሙበት አስበው ይገባሉ። ሲያመለክቱ እንደሱ ቢሉ እኛ ፈቃድ አንሰጣቸውም፤ ሁሉንም ሕብረተሰብ በእኩል እናገለግላለን ብለው ነው ፈቃድ የሚሰጣቸው፤ ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ግን መንሸራተት ያሳያሉ።

ወገንተኝነት ከሚዲያ ሙሉ ለሙሉ ይጠፋል ተብሎ ባይታሰብም፤ እኛ አገር እንዳለው ጭልጥ ያለ ወገንተኝነት፤ አንዱን እያሞገሱ፤ አንዱን እያኮሰሱ የሚሠራ ሚዲያ ግን ብዙም የለም።

ይህንን የመቆጣጠር ኃላፊነት እኮ የእናንተ ነው። እንህ ያደርጋሉ ባለችኋቸው ሚዲዎች ላይ ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?

ሁለት ነገሮችን ለማመዛዘን እንሞክራልን። ቸኩለን ወደ እርምጃ አንሄድም። ባንድ በኩል አሁን የተጀመረው የሚዲያ ነፃናትና ተደራሽነት መስፋት፤ የተለያዩ ድምፆች በሚዲያ የመስተናገዳቸው ጉዳይ እንዲቀጥል ስለምንፈልግ፤ አንዴ መስጠት፤ አንዴ መንፈግ እንዳይሆን ቸኩለን ወደ እርምጃ አንገባም። ቢያምም አንዳንድ ነገር መታገስን ይጠይቃል።

ስከምን ድረስ ነው መታገስ ሚቻለው?

ይገባኛል እመጣበታለሁ። እና ሁለተኛው ደግሞ ሕብረተሰብ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የሚዲያ አዘጋገቦች ሲኖሩ፤ ገና ለገና መማር አለብን እያልን ሕብረተሰቡን የሚጎዳ ቀጥተኛ ነገር ሲፈፀም ዝም አንልም።

ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የቁጥጥር ሥራ እየሰራን መዝግበን እየያዝን በየወሩ መጨረሻ በቁጥር የተደገፈ ሪፖርት ለየሚዲያ ተቋማቱ እንሰጣለን። እንዲታረሙበት ይዘቱንም አስመልክተን በዝርዝር ሪፖርት እንሰጣለን።

አንዳንዶቹ ቀና ምላሽ ይሰጡናል። አንዳንዶቹ ሙግት የሚገጥሙ አሉ። ግን በሂደት ሚዲያው በየጊዜው የሚሰራው ልምድ ይታያል። ያኔ የማያሻሽል ከሆነ በአካል እናነጋግራለን፤ ከዚያ በኋላ የማያሻሽሉ ከሆነ የማሳሰቢያ ደብዳቤም፤ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤም ይሰጣል።

ከዚያ የማገድ እና ፈቃድ የመሰረዝ የእርምጃ ሂደቶችን እንከተላለን። ስለዚህ አንቸኩልም እንጂ እርምጃ አንወስድም ማለት አይደለም።

ከዚህ በፊት በዚህ ሂደት ያለፉና እርምጃ የተወሰደባቸው ሚዲያዎች አሉ?

ደረጃው ይለያያል እንጂ ደብዳቤ የፃፍንባቸው ሚዲያዎች አሉ። አንዳንዴ ከግል፣ ከሕብረተሰቡ እንዲሁም ከመንግሥትም ጥቆማዎች ይደርሳሉ። ያኔ መጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ ይደረጋል። የመረጃ ትክክለኝነት በሌለበት ቦታ ላይ ደግሞ ይቅርታ እንዲጠይቁና የተስተካከለ መረጃ እንዲያስተላልፉ ይደረጋል። ይህ የየቀን ሥራችን ነው።

ከዚያ ባለፈ ግን ግጭት ቀስቃሽ የሆነ፣ አንድን ብሔር በሌላው ላይ የሚያነሳሳ ዓይነት፣ ሰላማዊ የሆነን የተቃውሞ መንገድ ከማስተዋወቅ ይልቅ ግጭት ቀስቃሽ የሆነ መንገድን ተከተሉ የሚል የሚዲያ ሪፖርትን አግኝተን ከባድ ማስጠንቀቂያ ጽፈንበታል።

የትኛው የሚዲ ተቋም ነው?

ሚዲያውን ለጊዜው መጥቀሱ ብዙ አስፈላጊ አይደለም። ምክንያቱም እኛ ዓላማችን ስም በመጥቀስ ማሳፈር [naming and shaming] ሳይሆን እንዲታረሙ ነው። ሚዲያውም ለእኛ ቀና ምላሽ ሰጥቷል። ተሳስተናል አንደግምም ብለዋል። አሁንም እየተከታተልን ነው፤ እንደሱ አይነት ፈር የለቀቁ ሪፖርቶች አልተደገሙም።

በፍርድቤት የተያዙ ጉዳዮች በሪፖርት መልክ በዘጋቢ ፊልም መልክ ቀርባሉ። ይህን በተመለከተ የፍርድ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ ሳድራሉግም አንፃር አግባብ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ?

የፍርድ ቤት ጉዳዮች አዘጋገብ መመሪያ እያዘጋጀን ነው። በባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት መመሪያ አልነበረንም። ከእውቀት ማነስም ይመጣል። ሁሉም ነገር ከክፋት ብቻ ላይሆን ይችላል ስህተቱ የሚፈፀመው።

የማን የዕውቀት ክፍተት? እንዲህ ዓይነት ነገሮች የሚተላለፉት በመንግሥት ሚመሩ ልምድ ላቸው ሚዲያዎች ጭምር ነው

እነሱም ሊሆኑ ይችላሉ። የመንግሥት፣ የሕዝብ የሚባሉትም ሚዲያዎች ስህተት ሊሰሩ ይችላሉ። ነገር ግን በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች ላይ፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ወንጀለኝነቱ በፍርድ ቤት ሳይረጋገጥ ቀድሞ ያን ሰው ወንጀለኛ አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም።

እናንተ ላፊነት አለባችሁ። ሙያውን ታውቁታላችሁይህንን ባሠራጩት ላይ ምን የወሰዳችሁት እርምጃ አለ?

በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ባልተገባ መልኩ ተዘገበ የሚል ለብሮድካስት ባለሥልጣን የቀረበ ቅሬታ የለም። ቅሬታ በሚቀርብበት ጊዜ እሱ ላይ ተመስርተን ተጨማሪ ምርመራ እናደርጋለን።

በቅርብ፤ ሦስት ወር ገደማ ቢሆነው ነው የጀመረውና በመደበኛነት በምናደርገው የቁጥጥር ሥራ ናሙና ወስደን ነው የምናከናውነው እንጂ ሁሉንም ሚዲያዎች 24 ሰዓት፤ ሰባቱንም ቀን የቁጥጥር ማድረግ አቅሙ የለንም። አንዳንድ ነገሮችን ልንስት እንችላለን።

ለምሳሌ ሜቴክ ላይ ተፈፀመ ተባለውን ሙስና ቅሌትን ያቀረበ ዘጋቢ ፊልም ከአንድ በላይ ሚዲዎች ላይ ያውም በተመሳሳይ ሰት መዘገቡ ይታወሳል። ይንን ብይ ዘገባ ትስቱታላችሁ አላስብም።

እሱ በተላለፈበት ጊዜ እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበርኩ። በዚያ ሰዓት ከመምህራን ጓደኞቼ ጋር ስናወራ የዘጋቢ ፊልሙ ተገቢነት ብዙም አልታየንም፤ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ገብቶናል። እንደ አስተማሪም ተወያይተንበታል።

ብሮድካስት ባለሥልጣን ከመጣሁ በኋላ ያወቅኩት በወቅቱ እሱን የተመለከተ ቅሬታ አልነበረም። መቀለ ላይ በነበረን ሕዝባዊ ስብሰባ ይሄው ሃሳብ ተነስቶ ትክክለኛ ነው ብዬ እንደማላምን ነግሬያቸዋለሁ።

"የግሉ ሚዲያ ላይ ስጋት አለኝ" መሐመድ አደሞ

ጋዜጠኞች ስለ ለውጡ ማግስት ሚዲያ ምን ይላሉ?

ባለሥልጣኑ ለምን እርምጃ አይወስድም ብለው ሲሉ። በብሮድካስት ሕግ መሠረት 6 ወር ውስጥ ቅሬታ ካልቀረበበት አንድ ፕሮግራም ሚዲያውም ዶክመንት አድርጎ የመያዝ ግዴታ የለበትም።

ባለሥልጣኑም መረጃን ቢበዛ ለስድስት ወር ነው ማስቀመጥ የሚችለው። እንደውም እዚህ አገር አጭር ነው፤ ሦስት ወር ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ቅሬታ ካልቀረበ በስተቀር ከዚያ በኋላ ቅሬታ ሊቀርብበት አይችልም። ታሪኩም ወደ ኋላ እየተጠቀሰ እርምጃ ሊወሰድ አይችልም ሥልጣኑም አይፈቅድለትም።

ብሮድካስት ባለሥልጣን የሚቆጣጠረው ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎችን ብቻ ነው። በእነዚህ ጣቢያዎች በዲጂታል [ማህበራዊ ሚዲያና ድረ ገፅ] የሚተላላፉትን ይዘቶች ማን ነው የሚቆጣጠረው?

እንኳን የኦንላይን ይቅርና የጋዜጣም ይዘት አንቆጣጠርም። ፈቃድ የምንሰጠውን ብቻ ነው የምንቆጣጠረው።

የብሮድካስት አዋጅ 533/99 ላይ እንድንሠራ የተሰጠንን ሥራዎች መሥራት ነው የምንችለው፤ ከዚያ ወጥተን መሥራት አንችልም። ያ ሥልጣን ስለሌለን በኢንተርኔት ላይ የሚተላለፉ ይዘቶችን በተመለከተ ችግሩ ቢገባንም ኢትዮጵያ ግን የሕግ ማዕቀፍ የላትም።

ምን አልባት አሁን በፓርላማ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ያለ የሀሰተኛ መረጃ እና ጸረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ አለ። አዋጁ ጸድቆ በሚወጣበት ጊዜ እሱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የሚሰጣቸው መሥሪያ ቤቶች ይኖራሉ። ምን አልባት ወደ ብሮድካስት ሊመጣ ይችላል፤ አይታወቅም።

እንዲሁ እኛ ስለወደድን ተነስተን እንቆጣጠር ብንል በየትኛው ሥልጣናችሁ ነው? የምንባለው።

አንዳንድ አገራት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ ሕግ ካረቀቁ በኋላ ለመቆጣጠር ይሞክራሉ። ሌሎች አገራት ደግሞ ይህ ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ስለሆነ ቁጥጥር አያስፈልገውም ይላሉ።

ስለዚህ ክርክር ያለበት ዘርፍ ስለሆነ፤ አገር የምትወስደውን አማራጭ ሳትወስን አንድ ሥራ አስፈፃሚ ተቋም ለዚያ ኃላፊ ሊሆን፤ ሊጠየቅም አይችልም።

ለቴሌቪዥን ቢያዎች ወይም ለሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሲሰጥ ሊያካትቷቸው ሚገቡ መረጃ ማስተላለፊያ መንገዶች ተለይተው ተቀምጠዋል?

የለውም። ቴክኖሎጂው እየቀደመን ነው። የእኛ ሕግ የተረቀቀው በ1999 ነው። ሕጎቹ እነዚህን ሊያካትቱ አይችሉም። እኛ ፈቃድ በምንሰጥበት ጊዜ፤ በሬዲዮ የሚሠራጭ፣ በቴሌቪዥን የሚሠራጭ ይዘት ብለን ነው። እውቅና የምንሰጠውም፤ ፈቃድ የምንሰጠውም ለዚያ ነው።

ሕጉ ይዘቶቻቸውን በምን ሌሎች ማሠራጫ ያሰራጫሉ ብሎ ገምቶ፤ እሱን ባካተተ መልኩ አልተቀረፀም። ሕጉም በመከለስ ላይ ነው፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል። የብሮድካስት አዋጁና ሐሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ሕግ ከጸደቀ ተጋግዘው ይህንን ዘርፍ መቆጣጠር ይችሉ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ያለዎት ተስፋና ሥጋት ምንድን ነው?

ብዙ ተስፋ አለ። በመንግሥት በኩል የታየው ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት መልካም ነው። ነገር ግን ሁሉን ነገር እናውቃቸዋለን፣ ይዘነዋል፣ ለዚያም ዝግጁ ነን ማለት ደግሞ አይቻልም።

ስጋቶቹ የሚመጡት የበዛ ወገንተኝነት የሚታይባቸው ሚዲያዎች አሉ። እንደ ትግል ሚዲያና አንድን ወገን ሃሳብ ሊያስፈፅሙ እንደተቋቋሙ ራሳቸውን የሚያዩ አሉ። እኔ 'የትግል ሚዲያ' የሚል ፈቃድ አልሰጠንም እላለሁ። የምንሰጠው ፈቃድ ሦስት ዓይነት ነው።

የፐብሊክ፣ የንግድና የማህበረሰብ ሚዲያ ፈቃድ ነው የምንሰጠው። የትግል ፈቃድ እኛ ሰጥተን አናውቅም። እና ራሳችሁን ከዚህ ቆጥቡ የሚል ነገር እናደርጋለን።

ራሳቸውን ግን ለአንድ ወገን፣ ለአንድ ፖለቲካ አላማ፣ ለአንድ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ጠበቃ አድርገው ሊያቆሙ የሚወዱ ዓይነት ሚዲያዎችን እያየን ነው። አሁን ሕብረተሰቡም እንደዚህ ዓይነት ሚዲያዎችን እየለያቸው ነው። እየከሰሙ ይመጣሉ የሚል ተስፋ አለን።

ይህ መለወጥ መቻል አለበት። ለጊዜው ያለው ትዕግስትም ያበቃል ብዬ አስባለሁ። ሕብረተሰብ እየተቆጣ ይሄዳል። መንግሥትም ደግሞ ሕብረተሰብን የመስማትና ሕግን የማስፈፀም ኃላፊነት አለበት።

ኃላፊነቱን በሚወጣበት ጊዜ ነገሮች እንዳይከብዱ ከወዲሁ ሚዲያዎቹ ራሳቸውን እያስተካከሉ ሙያዊ በሆነ፣ በእውነት ላይ የተመሠረተ፣ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መዘገብን ማዳበር አለብን።

የምርጫ አዘጋገብ

ዶ/ር ጌታቸው የዘንድሮውን ምርጫ አዘጋገብም በተመለከተ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረጉ እንደሆነ ነግረውናል። በምርጫ አዘጋገብ ዙሪያ በተለያዩ ዙሮች ጋዜጠኞች ሥልጠና እየተሰጣቸው ነው። መመሪያዎችም ተዘጋጅተዋል።

በምርጫ ቦርድ ይህ መመሪያ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በምርጫ ወቅት የጋዜጠኞችና የሚዲያ ሥነ ምግባር ምን መምሰል አለበት፣ ጋዜጠኞች ማወቅ ስላለባቸው የምርጫ ሂደቶች፣ የሚከለከሉና የሚፈቀዱ ጉዳዮችን የሚመለከት መመሪያ ተዘጋጅቷል። ይህ ሲፀድቅም ይህንን ተከትሎ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የአገር ውስጥም የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም ሥልጠና እየሰጡ እንደሚገኙም አክለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ