የሦስቱ አገራት መሪዎች የጋራ የጸጥታ ስጋቶቻቸውን ለመቀልበስ እቅድ አወጡ

የኤርትራው ፕሬዝድንት ኢሳያስ አፍወርቂ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ

የፎቶው ባለመብት, @hawelti

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፍወርቂ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በአሥመራ ተገናኝተው መክረዋል።

ሦስቱ መሪዎች በጸጥታ እና በልማታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተነግሯል።

በጸጥታው ረገድ ሦስቱ አገራት በሽብር፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ፣ የሰዎች እና እጽ ዝውውር ስጋቶችን አብሮ ለመዋጋት እቅድ ማውጣታቸውን የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚንስቴር አስታውቋል።

የሦስቱ አገራት መሪዎች 2018 ላይ የተፈራረሙትን የሦስትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የሦስቱ አገራት መሪዎች በየሃገራቸው ስላለው ሁኔታ፣ የሦስቱ አገራት ትብብር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የልማት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በዝርዝር መወያየታቸውን የኢንፎርሜሽን ሚንስትሩ በድረ-ገጹ አስነብቧል።

ሦስቱ መሪዎች 2020 የሦስቱ አገራት ጥምረት የሆነ በቀጠናው ሰላም፣ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ እድገትን የሚያጠናክር እቅድ መቅረጻቸው ተነግሯል።