የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ኮሮና ቫይረስን 'ሊያመርቱ' ነው

ቫይረሱ

የፎቶው ባለመብት, PETER DOHERTY INSTITUTE FOR INFECTION AND IMMUNITY

የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች ከቻይና ውጭ ለመጀመርያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስን ቅጂ ለማባዛት ጫፍ ደርሰዋል። ይህ ከተሳካ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ይበል የሚያሰኝ ተስፋ ይሰጣል ተብሏል።

ውጤቱም የዓለም ጤና ድርጅት እንዲያውቀው ይደረጋል። በሂደትም የቫይረሱን ባህሪ ለማወቅና ብሎም ለማከም ተስፋ ሰጪ ሙከራዎች ይኖራሉ።

የቻይና ሳይንቲስቶችም የቫይረሱን ቅጂና ዘረመላዊ ሂደቱን ማወቅ የቻሉ ሲሆን ቫይረሱን ራሱን ግን መፍጠር አልቻሉም።

እስከዛሬ ኮሮና ቫይረሱ 132 ሰዎችን የገደለ ሲሆን 6ሺ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ታውቋል።

ከቻይና ውጭ ደግሞ በትንሹ በ16 አገሮች 47 ሰዎች ቫይረሱን እንደተሸከሙ ተረጋግጧል። ከነዚህ አገሮች መሀል አሜሪካ፣ ፈረንሳይና አውስትራሊያ ይገኙበታል።

በሜልበርን፣ የሚገኙት ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ቫይረሱን የቀዱት አንድ በቫይረሱ ከተጠቃ ግለሰብ ነው። ናሙናው የተላከላቸውም ባለፈው አርብ ነበር።

'ለእንዲህ አይነት የቫይረስ ክስተት ለረዥም ዘመን ስንዘጋጅበት ነበር። ለዚህም ነው በፍጥነት ቫይረሱን ቅጂ ማምረት የቻልነው' ብለዋል የጥናት ቡድኑ ኃላፊ።

የቫይረሱ ቅጂ መገኘቱ ምን ፋይዳ ይዞ ይመጣል?

ሐኪሞች እንደሚሉት ቫይረሱ ቅጂ መመረቱ በሙከራ ጥናት ውስጥ የቁጥጥር ናሙና (ኮንትሮል ማቴሪያል) ሆኖ ያገለግላል። ይህም ማለት በሽታን ለማከም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።

በተለይ የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት ያልጀመሩና ነገር ግን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለመለየት አጋዥ ነው።

የቻይና ባለሥልጣናት እንዳረጋገጡት ቫይረሱን አስቸጋሪ ያደረገው ልክ እንደ ጉንፋን ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ መተላለፉና ገና ወደ ሙሉ በሽታ ሳያድግ መሠራጨቱ ነው።

የቫይረሱ ቅጂ መመረት መቻሉ በተለይ የሙከራ ክትባትን ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ እርምጃ ነው እየተባለ ነው።

የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት እንደሚለው ኮሮና ቫይረስ ራሱን እስኪያጎለብት ከ2 እስከ 10 ቀናት ይፈጅበታል። በዚህ ጊዜ ወደ ሌላ ሰው መሰራጨት መቻሉ ነው አሁን ችግር እየፈጠረ ያለው።

አውስትራሊያ ዛሬ እንዳስታወቀችው 600 ዜጎቿን ከዉሃን ግዛት በማውጣት በክሪስማስ ደሴት ለብቻቸው ለማስቀመጥ ተዘጋጅታለች። ክሪስማስ ደሴት ከአውስትራሊያ በ2ሺ ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ናት።