ህንድ ውስጥ 20 ሕጻናትን ያገተው ግለሰብ ተገደለ

አጋቹ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Image copyrightDEEPAK KUMAR SRIVASTAVA

ለአንድ ዓመት ልጁ የውሸት የልደት በዓል በማዘጋጀት ከ20 የሚበልጡ ልጆችን ያገተው አባት በፖሊስ ተገደለ።

በድርጊቱ የተበሳጩ በህንዷ ሁታርፕራዲሽ ግዛት ውስጥ የሚገኘው ፋሩቅአባድ አካባቢው ነዋሪዎች ሚስቱን ደብድበው ገድለዋታል።

ሱባሐሽ ባታም የተባለው አባት ቀደም ሲል በግድያ ወንጀል ተከሶ የነበረ ሲሆን ከእስር የወጣውም በዋስ ነው።

እገታውን ተከትሎ ፖሊስ ግለሰቡ እጁን እንዲሰጥ ለ10 ሰዓታት ለማሳመን ጥረት ቢያደርግም ምንም ሃሳቡን ሊቀይር ባለመቻሉ አጋቹን ፖሊስ ተኩሶ ገድሎታል።

ሰውዬው ያገታቸው ከ6 ወር እስከ 15 ዓመት የሚደርሱ ታዳጊዎች ግን ሁሉም በሰላም ተገኝተው ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥተዋል።

ሰውየው ልጆቹን አግቶ አሻፈረኝ በማለቱ ቤተሰቦች "ልጆቻችንን አንድ ነገር ያደርግብን ይሆን" በማለት ተሸብረው እንዳደሩ በስፍራው የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።

"ፖሊስ ለብዙ ሰዓታት እጁን እንዲሰጥ ተደራድሮታል። ይህ ጥረት ባለመሳካቱም ሌላ ኃይል እንዲጨመር ተደርጓል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ቤተሰቦች ከበው እያዩ ስለነበር ልጆቻችንን ይገድልብናል በማለት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሆነው ሌሊቱን ያለ እንቅልፍ ነው ያሳለፉት" ብሏል።

የሚገርመው ሰውየው ያገተው ለግብዣው የጠራቸውን ሕጻናት ብቻ ሳይሆን ባለቤቱንና የራሱንም ልጅ ጭምር ነበር።

የፎቶው ባለመብት, DEEPAK SRIVASTAVA

ግለሰቡ እገታውን የፈጸመው ቀደም ሲል በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ እንዲታሰር ያደረጉት የአካባቢው ሰዎች ናቸው ብሎ ስላመነ ይህንን ለመበቀል እነደሆነ ተነግሯል።

20ዎቹን ልጆች አግቶ የአካባቢው ሰዎች ቢለምኑት ያስቸገረው አጋቹ በሰባተኛው ሰዓት ላይ አንዲት የስድስት ወር ልጅ እንድትወጣ አድርጓል።

ከዚያ በኋላ የአካባቢው ሰዎች ለፖሊስ አመለከቱ። ፖሊስ መምጣቱን ሲያይ ግለሰቡ ከውስጥ ሆኖ መተኮስ ጀመረ።

በዚህም አልበቃው ብሎ "ቦምብ አፈነዳለሁ" እያለ ማስፈራራት በመጀመሩ ፖሊስ ሌሎቹን ለማዳን ሲባል እርምጃ መውሰድ ስለነበረበት ሰውየው እንደተገደለ ፖሊስ አረጋግጧል።

በተኩስ ልውውጡም ሁለት የፖሊስ አባላትና የአጋቹ ሚስት ቆስለዋል። ኢንዲያ ቱዴይ ባወጣው መረጃ መሰረት አጋቹ ለአካባቢው አስተዳደር ደብዳቤ ጽፎ ነበር። በደብዳቤውም ቤቱ የመጸዳጃ ቤት ችግር እንዳለበትና መንግሥት የተሻለ ቤት እንደነፈገው ገልጾ ነበር።

ታዲያ ሰዓታትን ባስቆጠረው የአጋች ታጋች ድራማ በርካታ የህንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ባታም የሚፈልገውን መንግሥትም ሆነ ግለሰቦች እንዲያሟሉለት እና ያገታቸውን 20 ሕጻናት ሲጠይቁት እንደነበር ተዘግቧል።