ሩዋንዳና ኡጋንዳ እስረኛ ለመቀያየር ተስማሙ

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒና የሩዋንዳ አቻቸው ፖል ካጋሜ

የፎቶው ባለመብት, Yoweri K Museveni twitter page

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒና የሩዋንዳ አቻቸው ፖል ካጋሜ በሃገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ላይ መክረዋል።

በሃገራቱ መካከል የተከሰተው ውጥረት ተካሮ ድንበራቸውን ለመዝጋት ተገደዋል።

መሪዎቹ የተገናኙት በትናንትናው ዕለት በአንጎላዋ መዲና ሉዋንዳ ሲሆን በአንጎላው መሪ ጆዋዎ ሎውሬንኮ መሪነት ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው ጉባኤ ነው። በዚህ ጉባኤ የኮንጎው ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሺሰከዲም ተገኝተዋል።

ሙሴቪኒና ካጋሜ ሁለቱም ሃገራት ባላንጣ የሚሏቸውን ሃይሎች በገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ፣ ስልጠና ከመስጠት እንዲታቀቡ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከጉባኤው በኋላ የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል በመከሩበት በዚህ ጉባኤ ሰላም እንዲመጣ አበክረው ለመስራት እንዲሁም እስረኞች ለመቀያየር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ምን ያህል እስረኞች እንደሚቀያየሩ፣ ጊዜውስ መቼ ሊሆን ይችላል የሚለው ላይ ዝርዝር ከመስጠት መቆጠባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ሁለቱ መሪዎች ቀጣዩ ጉባኤም በሁለቱ ሃገራት መካከል በምትገኘው ካቱና፣ ጋቱና ድንበር ለማካሄድ ቀን ቆርጠዋል።

የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ከተቋረጠ አመት ያለፈ ሲሆን፤ የሩዋንዳ ባለስልጣናት ተቃዋሚውን ርዋንሳ ናሽናል ኮንግረስን ትደግፋለች በማለት ኡጋንዳን ይወነጅሏታል።

ከዚህም በተጨማሪ የሩዋንዳ ዜጎችንም በማሰርና እንግልት ትፈፅማለች የሚሉ ስሞታዎች በተደጋጋሚ ከባለስልጣናቱ ይሰማሉ።

ኡጋንዳ በበኩሏ ሩዋንዳ በደህንነትና ፀጥታ ጉዳይ ላይ እንዲሁም በሃገሬ ፓለቲካ ውስጥ ጣልቃ ትገባለች ትላታለች።