የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው የዙማ ፎቶ እያነጋገረ ነው

ጃኮብ ዙማ

የፎቶው ባለመብት, @PresJGZuma

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የአገሪቱ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣባቸው በኋላ ወዲያውኑ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጠመንጃ ይዘው ሲያነጣጥሩ የሚያሳይ ፎቷቸውን መለጠፋቸው ውዝግብ ቀስቅሷል።

ዙማ ፍርድ ቤት መቅረብ በነበረባቸው የቀጠሮ ዕለት ስላልመጡ ነበር ማክሰኞ ዕለት የፒተርማርዝበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዙን ያስተላለፈው።

ጠበቃቸው ዙማ ስለታመሙ መቅረብ እንዳልቻሉ በመግለጽ በወቅቱም ለፍርድ ቤቱ መታመማቸውን የሚገልጽ የሐኪም ወረቅት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ ያወጣው የእስር ማዘዣው ተግባራዊ የሚሆነው ዙማ ስለጤናቸው ሁኔታ ያቀረቡት ማስረጃ ሐሰት መሆኑ ከተረጋገጠና ግንቦት ወር ላይ ፍርድ ቤት ካላቀረቡ ነው።

ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ቀንና ማብራሪያ የሌለውን ጠመንጃ ይዘው አንዳች ነገር ላይ ሲያልሙ የሚያሳውን ፎቷቸውን ትዊተር ላይ እንዲሰራጭ መለጠፋቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ምናልባትም ዙማ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት አለ በሚልም ትችቶች እየተሰነዘሩባቸው ነው።

የደቡብ አፍሪካ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት ፎቶው የተነሳው ክዋዙሉ ናታል ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ነው።

ዙማ ፍርድ ቤት ሙስናን፣ ማጭበርበርንና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ በበርካታ የወንጀል ድርጊቶች ክስ በመመስረቱ ነው ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው።

በርካታ የደቡብ አፍሪካ ዜጎችም በቀድሞው ፕሬዝዳንት ፎቶ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፤ ከእነዚህም መካከል "ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ደብዳቤ መታመምዎትን ነው፤ ወይስ የሐኪም ትዕዛዝ ማደን ነው?" የሚል ይገኝበታል።

"እንዳሉት ኩባ ወይም ፕሪቶሪያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል አልጋ ላይ አልነበረም እንዴ መገኘት የነበረብዎ?" ሲል ሌላኛው ጥያቄ አቅርቧል።

ሌሎች ደግሞ ዙማን የሚከላከሉ አስተያየቶችን በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ አስፍረዋል።