ኮሮናቫይረስ፡ በዉሃን ከሚገኙ ኢትዮጵያውን ተማሪዎች 95 በመቶ መመለስ ይፈልጋሉ

ዉሃን

የፎቶው ባለመብት, Barcroft Media

ኮሮናቫይረስ በቀሰቀሰባት ዉሃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች መንግሥትን 'ወደ አገራችን' ይመልሰን ሲሉ ለሁለተኛ ጊዜ ጠየቁ።

በዉሃን ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች 95 በመቶዎ የሚሆኑት መመለስ እንደሚፈልጉ በበተነው መጠይቅ ማረጋገጡን በዉሃን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ለቢቢሲ አስታውቋል።

የህብረቱ ፕሬዝደንት ዘሃራ አብዱልሃዲ እንደገለፀችው በመጠይቁ ከተሳተፉ ተማሪዎች መካከል 41 በመቶ የሚሆኑት መንግሥት ወጪያችንን ሸፍኖ ወደ አገራችን ይመልሰን ያሉ ሲሆን፤ 54 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በራሳችንም ወጪ እንመለሳለን መንግሥት ግን ጉዟችንን ያመቻችልን ሲሉ ፍላጎታቸውን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የተማሪዎቹን 'ወደ ኢትዮጵያ መልሱን' ጥያቄን ህብረቱ በቻይና ለኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዳቀረበ የምታስታውሰው ዘሃራ፤ አሁንም የተማሪው ጥያቄ እጅግ እየገፋ በመምጣቱ መጠይቅ በትነው የተማሪውን ወደ አገራችን መልሱን ጥያቄ በጥናት ማረጋገጣቸውን ታስረዳለች።

ዘሃራ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች፤ እንዲሁም የሟቾችም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በመጥቀስ "ተማሪው ከባድ የስነልቦና ጫና ውስጥ ነው ያለው" ትላለች።

በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥያቄ በቀረበለት ወቅት 'የተማሪዎቹን ጥያቄ ለመመለስ ሁኔታዎችን እያጤንን ነው' የሚል ምላሽ ለቢቢሲ ሰጥቶ ነበር።

በዉሃን የተማሪዎች ህብረት በጥናት የተደገፈውን የአሁኑን የተማሪዎች ጥያቄ ለኤምባሲው ያቀረበው ከአራት ቀናት በፊት እንደሆነ ዘሃራ ብትናገርም፤ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሽን መሪ አቶ ገነት ተሾመ ይህ መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ገነት ምንም እንኳ ይህ መረጃ የለኝም ይበሉ እንጂ ኤምባሲው በቀደመው ጥያቄው መሠረት ሁኔታዎችን እና ያሉ አመራጮቹን ማጤኑን እንደቀጠለ ተናግረዋል።

በዉሃን ሶስት መቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከትምህርት ውጭ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ይህ ነው የሚባል እንዳልሆነ ቢቢሲ ከኤምባሲው ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

ኮሮናቫይረስ ከተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ የሚመጡ መንገደኞችን በለይቶ ማከሚያ ለማስቀመጥ መወሰኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ማስታወቁ ይታወሳል።