ስዊዘርላንድ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚያወግዙ ዜጎቿን የሚቀጣ ሕግ ልታወጣ ነው

ስዊትዘርላንድ፤ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚያወግዙ ዜጎቿን ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስዊዘርላንድ ዜጎች፤ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚያወግዙ ሰዎችን የሚቀጣ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ድምፅ ሊሰጡ ነው።

ስዊዘርላንድ ውስጥ ሰዎችን በዘራቸውና በኃይማኖታቸው ማግለል በሕግ ያስቀጣል። አሁን ደግሞ የተመሳሳይ ፆታ አፍሪቃሪዎችን ማግለል ወንጀል ሊሆን ይችላል።

የስዊዝ ሴት አፍቃሪያን አባል የሆነችው አና ሮዘንዋሰር "ሃገራችን እጅግ የሠለጠነች ነችና ዜጎች መገለል አይደርስባቸው ብለው ያስባሉ፤ ግን ይህ እውነት አይደለም" ትላለች።

«ሃገራችን ሃብታም ልትሆን ትችላለች። ዘመናዊ ግን አይደለችም። ሰዎች በሚያፈቅሩት ፆታ ምክንያት መገለል ይደርስባቸዋል። ይህ ደግሞ የሕግ ከለላ ይፈልጋል።»

ስዊዝ ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ከሌሎች አምስት እጥፍ ራሳቸውን ያጠፋሉ። ይህ ደግሞ ምን ያህን መገለል እየደረሰባቸው እንደሆነ ማሳያ ነው ስትል አና ትሞግታለች።

ነገር ግን ተቺዎች ሕጉ የመናገር ነፃነትን ይጋፋል ሲሉ ቅዋሜያቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

የቀኝ ዘመሙ ስዊስ ሕዝቦች ፓርቲ አባሉ ቤኒያሚን ፊሸር «አሁን ስለ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ቀልድ መቀለድ እንቻል አንቻል እንኳን አናውቅም» ይላል።

«የመናገር ነፃነት ያለባት ሃገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ሊገልፁ ይገባቸዋል። አንዳንዴ አገላለፃቸው እሬት፣ እሬት ቢልም ልንቀበል ይገባል።»

አንዳንድ የኃይማኖት ተቋማትም አዲሱን ሕግ እየተቃወሙት ይገኛል። በሃገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች በርካታ ምዕመን ያሉት የስዊስ ኤቫንጀሊካል አላያንስ ቤተክርስቲያን ሕጉ ብዙ ያስደሰታት አትመስልም።

«በኛ ቤተክርስትያን ሕጋዊነት ያለው ጋብቻ በወንድና ሴት መካከል የሚደረግ ነው። እኛ ይህንን ሃሳባችንን በነፃነት መግለፅ እንፈልጋለን። ነገር ግን ሌሎች ዓይነት የጋብቻ ዓይነቶች ያገለልን መስለን መታየት አንፈልግም» ይላሉ የቤተክርስያኗ ኃላፊ ማርክ ጆት።

የሕጉ ደጋፊዎች ሰዎች በበኩላቸው "በምትሰጡት ግላዊ አስተያየት ስለማትቀጡ ስጋት አይግባችሁ" ይላሉ። ቅጣት የሚደርስባቸው በግላጭ መገለል ያደረሱና በደል የፈፀሙ ናቸው ተብሏል።

ስዊዘርላንድ ውስጥ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመሥረት ሕጋዊነት አለው። ጋብቻ መመሥረት የሚያስችል ሕግ በቅርቡ ይወጣል ተብሎም ይጠበቃል።

የስዊስ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በፍቅር ምርጫቸው ምክንያት ከመገለል አልፎ አካላዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ሕጉ ተቃውሞ ቢገጥመውም በበርካቶች ዘንድ ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚችል እየተገመተ ነው።