ከሞት የታደገው ጎሽ ከቤት አልወጣም ብሎት የተቸገረው ኢትዮጵያዊ

ጎሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወጣት ጋሻው ደመላሽ ነዋሪነቱ ኢሉ አባቦራ ዞን፤ ዳሪሙ ወረዳ አቡነ ጋሊ በምትሰኝ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በግብርና ሥራ የሚተዳደረው ጋሻው፤ ከአራት ዓመታት በፊት በሚኖርበት አካባቢ በጭቃ ተይዞ መንቀሳቀስ ያቃተው የጎሽ ግልገል ባጋጣሚ ይመለከታል።

ጥሎት ቢያልፍ የግልገሉ እጣ ፈንታ ሞት መሆኑን በመረዳቱ፤ የጎሹን ግልገል ጥሎ ማለፍ አልቻለም፤ ጎሹን ከጭቃ ለማስለቀቅ ግብግብ ያዘ።

ከዚያም ጎሹን ከጭቃ አስለቅቆ ወደ መኖሪያው ይዞት ይሄዳል።

"ወደ ቤት ይዤው ሄድኩ። አባቴን አስፈቅጄ አንገቱ ላይ ገመድ አስሬ የላም ወተት እያጠጣሁት ማሳደግ ጀምርኩ" ይላል ጋሻው።

የጎሹን ግልገል በአካባቢው የሚያገኛቸውን የተለያዩ ነገሮች እየመገበ እንዳሳደገ ጋሻው ይናገራል። "... እንጀራ፣ አሞሌ ጨው፣ የአረቄ አተላ፣ ማር ሁሉ አበላው ነበር። ከዛ በፍጥነት አደገ ከዛ ተላመደ" ይላል።

በአጋጣሚ ህይወቱን አትርፎ ያሳደገው የጎሸ ግልገል ግን በትላልቅ ቀንዶቹ የሰፈሩን ሰው እና የቤት እንስሳት ለማሸበር የወሰደበት ጊዜ አጭር ነበር።

"አሁን ስላስቸገረ ታስሮ ነው የሚውለው። ሰው እና ከብቶችን መውጋት ሲጀምር ነው ማሰር የጀመርኩት። ከዛ በፊት ከከብቶች ጋር ነበር ተሰማርቶ የሚውለው። ከእኔ ውጪ ሁሉንም ሰው እና ከብቶች እየወጋ ሲያስቸግር ለመጣል ወሰንኩ። እርቆ ወደሚገኝ ጫካ ወስጄ ብተወውም ተመልሶ መጣ። እንደገና ብወስደውም ስለተላመደ ተመልሶ መጣ" በማለት ጋሻው ጎሹን ወደ ጫካ ወስዶ ለመጣል ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ያስረዳል።

አመጸኛውን ጎሸ ጠምጄ ለማረስ ሞክሬ ነበር የሚለው ጋሻው፤ የአከባቢው ኃላፊዎች የዱር እንስሳ በመጠቀም ማረስ እንደማይችል በመግለጽ ክልክላ እንዳደረጉበት ይናገራል።

"በጣም ነው የሚያርሰው፤ የትኛውም በሬ እንደ ጎሹ አያርስም። ከቀበሌ እየመጡ የዱር እንስሳ አጥምደህ ማረስ አትችልም ሲሉኝ ነው የተውኩት።"

ጎሹን መጠቀምም ሆነ ከቤቱ ማስወጣት ያልቻለው ጋሻው፤ ለዱር እንስሳው ቀለብ መስፈር ቢበዛበት፤ ከገባበት ጣጣ መንግሥት እንዲገላግለው በአካባቢ ይመለከታቸዋል ላላቸው የመንግሥት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች አቤት ቢልም መፍትሄ አለማግኘቱን ይናገራል።

"በዞን እና በወረዳ ላሉት አሳውቂያለሁ። ከብት እርባታ ለሚባሉትም ነግሬያቸዋለሁ። ይሄው ስንት ግዜ ደብዳቤ ይዤ፣ ስንት ቦታ ተመላለስኩ፤ መፍትሄ የሚሰጠኝ ግን ላገኝ አልቻልኩም። እየመጡ ፎቶ አንስተው ይሄዳሉ እንጂ ምንም የረዱኝ ነገር የለም" ይላል።

የኦሮሚያ ክልል የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ጨመረ ዘውዴ፤ የዱር እንስሳትን ማልመድም ሆነ በመኖሪያ ቤት ውስጥ አስሮ ማስቀመጥ በህግ የተከለከለ ተግባር ነው ይላሉ።

አቶ ጨመረ እንደ ጎሽ ያሉ የምግብ ፍጆታቸው ከፍተኛ እና አደገኛ የዱር እንስሳትን የማላመድ ተግባር ከዚህ ቀደም ገጥሟቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ።

"በቅድሚያ እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞን አያውቀውም። ይሄን ጎሽ እንዴት ማላመድ እንደጀመረ አላወቅንም። ግን ይዘው ካቆዩት በኋላ አድጎ የዱር እንስሳነት ባህሪው ሲመጣ ነው ለእኛ ያሳወቁን። ይህን መሰል ተግባርም የተከለከለ ስለመሆኑ በሃገሪቱ ህግ ላይ ሰፍሯል"

አቶ ጨመረ ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ያሉትን ሁለት ሃሳብ ያስቀምጣሉ፤ ጎሹን ወደ ጫካ ለመመለስ ጥናት ማካሄድ አልያም ደግሞ ጎሹ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ከሆነ እርምጃ መውሰድ።

"እንዲህ አይነት የዱር እንስሳ ወደ ጊዜያዊ ማቆያ መውሰድ አይችልም። ከሰዎች ጋር የተላመደን የዱር እንስሳ ወደ ጫካ ይመለስ ከተባለ በጫካ የመኖር ባህሪውን አጥቷል። ስለዚህ ጎሹ ስለሚገኝበት ሁኔታ ማጥናት ግድ ነው። አለበለዚያ ግን ጎሹ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ከሆነ እርምጃ መውሰድ የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል" ይላሉ።