ኦነግና ኦፌኮ አባሎቻችን እየታሰሩብን ነው ሲሉ ተናገሩ

ካቴና እስር ቤት በር ላይ Image copyright Getty Images

በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተጽእኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር-ኦነግ አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ እየታሰሩ ነው ሲሉ አቤቱታቸውን አቀረቡ።

የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ቦረን ትናንት አርብ፣ ረፋድ ላይ ፓርቲያቸው በሰጠው መግለጫ ላይ "ከ350 በላይ የሚሆኑ አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን ለእስር ተዳርገውብናል" ብለዋል።

"ከሰሞኑ ደግሞ በበርካታ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ እኛ በማናውቅም ምክንያት አባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ እየታሰሩ ይገኛሉ።"

ይህ የጅምላ እስር እየተጠናከረ እየሄደ ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አከባቢዎች ነው ሲሉ ያክላሉ አቶ ሚካኤል።

ባሳለፍነው አንድ ሳምንት ብቻ በ7 የኦሮሚያ ዞኖች የሚገኙ 350 አባሎቻችን እና ደጋፊዎቻችን በጅምላ የታሰሩ ሲሆን፤ ይህን የጅምላ እስር እያደረገ ያለው ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን አውቀናል ሲሉ ይከስሳሉ።

በተመሳሳይ መልኩ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ- ኦፌኮ ፓርቲም ደጋፊዎቼ እና አባላቶቼ ለእስር እየተዳረጉብን ነው ብሏል።

የፖርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጥሩነህ ገምታ በቅርቡ 27 አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ለእስር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

"በጥቅሉ 27 ሰዎች ታስረዋል። 23 አባላት እና 4 ደጋፊዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች የት ናቸው ቢባል፤ ጉጂ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢ ከተማ፣ የኦፌኮ ወጣት ሊግ ፊቼ ከተማ ላይ ዱጎምሳ የሚባል አባላችን ታስሯል። ሰበታ ላይ ብቻ 11 ሰዎች ታስረውብናል። ይህ እስር የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን ያሳያል" ይላሉ።

ኦሮሚያ ፖሊስ ለቀረበበት ወቀሳ ምላሽ እንዲሰጥ ሙከራ ብናደርግም ልናገኛቸው አልቻልንም።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ግን በፖለቲካ ተሳትፏቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች ስለመኖራቸው የማውቀው ነገረ የለም ብለዋል።

"በክልላችን የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለሆነ ብቻ ማንም ሰው አይታሰረም መታሰርም የለበትም።

በሌላ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የታሰሩ ካሉ እሱን በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው አካል ማጣራት ያስፈልጋል ሲሉ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ለእስር የታደረጉት ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ የፖለቲካ ተሳትፎ ላይኖራቸውም ይችላል ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"የታሰሩበት ምክንያት በፖለቲካ ተሳትፏቸው ይሁን በሌላ ማወቅ በማይቻልበት ላይ እኔም ይህ ነው ማለት አልችልም።" በማለት ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፤ ለሀገሪቱ ደህንነት ሲባል ከዚህ በኋላ ማናቸውንም በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ አካላት አልታገስም ማለቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ወንጀል ተፈጽሞባቸው በነበሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ቁጥጥር ሥር እያዋለ እና ክስ እየመሰረተ መሆኑንም አስታውቋል።

በመግለጫው ላይ በግጭቶቹ ላይ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ከሚገኙባቸው ስፍራዎች መካከልም ምዕራብ ጉጂ፣ አዳማ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ እና አዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን፣ የተጠቀሱ ሲሆን ከደቡብ ክልል ደግሞ ጌዲኦ ዞን፣ ሐዋሳ፣ የቴፒና ሸካ ዞን ተጠቅሰዋልወ።

በመግለጫው ላይ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ የተጀመረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም የተጠቀሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከልም በሶማሌ ብሔራዊ ክልል በጅግጅጋና ሌሎች ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል ካማሽ ዞን፣ መተከል ዞን የተጠቅሰዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላት እና ደጋፊዎች እስር ግን ከዚህ ከጠቅላይ አቃቢ ሕግ እርምጃ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ ግልጽ አይደለም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ