የሶማሊያዊው ጋዜጠኛ መገደል ቁጣን ቀሰቀሰ

የሶማሊያ ሰንደቅ አላማ

የፎቶው ባለመብት, STUART PRICE

ሶማሊያዊው ጋዜጠኛ አብዲዋሊ አሊ ሃሰን መገደል ቁጣን ቀስቅሷል።

ጋዜጠኛው ሞቃዲሾ አካባቢ በምትገኝ ከተማ የተገደለ ሲሆን ሁኔታውንም ጋዜጠኞች ክፉኛ እያወገዙት ይገኛሉ።

የሶማሊያ ጋዜጠኞች ማህበር እንዳስታወቀዉ ማንነታቸው ያልተገለፀ ታጣቂዎች ጭንቅላቱ ላይ እንዲሁም ደረቱ ላይ ብዙ ጊዜ ተኩሰውበታል።

አፍጎዬ በምትባል ከተማ ነዋሪነቱን ያደረገው አሊ ሃሰን ከስራ ወደቤቱ ሲመለስ ነው ጥቃቱ የተፈፀመበት። ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ ግን እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም ተብሏል።

ጋዜጠኛው የሚሰራበት ሬድዮ ጣቢያ መንግሥትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚተች ሲሆን፤ አብዲዋሊም የሰላ ትችትን በመሰንዘር ይታወቃል።

በቅርቡ የሶማሊያ ጦር የሚያደርጋቸውን ዘመቻዎች አስመልክቶ የተለያዩ ዘገባዎችን እያቀረበ ነበርም ተብሏል።

የስራ ባልደረቦቹ ከስራዎቹ ጋር ተያይዞ በርካታ የሞት ማስፈራሪያዎች እንደደረሱት የገለፁ ሲሆን፤ በተለይም በባለፈው ዓመት ይህ ሁኔታ መጠናከሩን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሃገሪቱ ውስጥ ያለው የፕሬስ ነፃነት ባለፉት ሶስት ዓመታት ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ መምጣቱን በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው ሪፖርቶች አሳውቋል።

በተለይም ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ወይም ፋርማጆ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ እየተባባሰ መምጣቱም ተዘግቧል።

በነዚህ ዓመታትም ቢያንስ ስምንት ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አምስቱ በአልሻባብ ጥቃት፣ ሁለቱ በማይታወቁ ታጣቂዎች፣ አንደኛው ደግሞ በፖሊስ ተተኩሶበት ነው።