የህዳሴ ግድብ ድርድሮች ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ውይይት ተካሄደ

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, OFFICE OF THE PRIMEMINISTER FACEBOOK PAGE

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ በዋሽንግተን ለቀናት ሲካሄድ የነበረው የሶስቱ አገራት ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተገኙበት ስላሉት ድርድሮች አካሄድ እና አቅጣጫ ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተካሂዷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በፌስቡክ ገፁ እንዳስታወቀው ሚኒስትሮች፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎችም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦችን በውይይቱ ተሳትፈዋል።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሕግና ቴክኒክ ባለሙያዎች በዋሽንግተን ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ያለምንም ስምምነት መጠናቀቁን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍጹም አረጋ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ይሳተፉበታል የተባለውን ይህን ድርድር ያለውጤት እንዲያበቃ ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆነ አምባሳደር ፍጹም ያሉት ነገር የለም።

ቢቢሲ ለውይይቱ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች እንደተረዳው ምንም እንኳን የሚካሄደው ውይይት በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጥረት እያደረገች ቢሆንም በግብጽ በኩል ድርድሩ የውሃ ድርሻ ላይ እንዲያተኩር ግፊት እያደረገች ነው ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, OFFICE OF THE PRIMEMINISTER FACEBOOK PAGE

በሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የቆየው የህዳሴ ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ መሄዱን እኚሁ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን በመጠቆም አሁን ላይ ጉዳዩ "4 ለ 1" ሆኗል በማለት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑንም ምንጫችን ተናግረዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የድርቅ ማካካሻ ላይ የተዘጋጀውን ረቂቅ ሰነድም ኢትዮጵያ እንድትፈርም አሜሪካና የአለም ባንክ ጫና እያደረጉ መሆናቸውን እየተነገረ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፓምፒዮ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ አህመድ ጋር በረቂቅ ሰነዱ ላይ እንደሚወያዩ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ነው።