ኢትዮጵያዊቷ ከኤርትራዊት ጎረቤታቸው ከ20 ዓመት በፊት የተረከቡትን መለሱ

ወ/ሮ ሻሺቱ ንጉሴና ወ/ሮ ምግብ ተመስገን

የፎቶው ባለመብት, Shashe Neguse

ወ/ሮ ሻሽቱ ንጉሤ ጠይም፣ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። መጀመሪያ ቀበሌ ሦስት ነዋሪ የነበሩት፤ በኋላ ላይ ግን አዚያው ጎንደር ውስጥ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤት ገዝተው ገቡ። በወቅቱ የፍርድ ቤት ሠራተኛ ነበሩ።

ያኔ የፎገራ ሆቴል ገንዘብ ያዥ የነበሩት ኤርትራዊቷ ወ/ሮ ምግብ ተመስገን ደግሞ ቀድሞ ከሚኖሩበት ቀበሌ አራት፣ መሬት ተመርተው እዚያው ደብረብርሃን ሥላሴ ቤት ሠሩ። የሁለቱ ሴቶች ጉርብትናም የተመሠረተው ያኔ ነበር።

አዲስ ሠፈር አዲስ ጉርብትና ቢሆንም በበዓል መጠራራት የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በጋራ መከወን የተለመደ ነበር ይላሉ ወ/ሮ ምግብ።

ጉርብትናቸው ብዙም ሳይጠነክር፤ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ለያያቸው። ወ/ሮ ምግብ ሦስት ወልደው ያሳደጉበት፣ ከጎረቤቶቻቸው ክፉ ደግ ያዩበት ቤትን ጥሎ መሄድ ከባድ እንደነበር ይናገራሉ።

ወ/ሮ ምግብ ጎንደር ለ26 ዓመታት ያህል ኖረዋል። ኢትዮጵያዊ አግብተው ወልደው ከብደዋል። በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ኤርትራዊያን ወደ አገራችው ግቡ በተባለው መሠረት ቤት ንብረታቸውን ትተው ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው አገራቸው ገቡ።

በርግጥ ይላሉ ወ/ሮ ሻሺቱ፣ ወ/ሮ ምግብ ቀበሌ ሦስት ሲኖሩ አበልጆች ነበሯቸው። ቀበሌ አራትም ሲኖሩ የሚያውቋቸው ወዳጆች ብዙ ነበሩ።

ነገር ግን እቃ መሸከፍ ሳይቻል በድንገት ከአገር እንዲወጡ ሲደረግ ንብረታቸውን አደራ ብለው የሄዱት በቅርብ ጊዜ ለሚያውቋቸው ወ/ሮ ሻሽቱ ነበር።

ወቅቱ ጭንቅ ስለነበር ወ/ሮ ምግብ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ነበርና ጥለው የወጡት እቃቸውን መልክ መልክ ማስያዝም የወ/ሮ ሻሽቱ ኃላፊነት ነበር። የቤት እቃዎቻቸው የተወሰኑት ተሸጠው አዲስ አበባ ለሚገኙት እህታቸው እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ለቀረው ልጃቸው እንዲሰጥላቸው አደራ አሉ፤ ወ/ሮ ምግብ።

ይህንን ለማድረግ ወ/ሮ ሻሺቱ አደራ ተቀብለው በአግባቡ መከወናቸውን ይናገራሉ።

አደራውን የሠጧቸው ከአገር እንዲወጡ በተደረገበት ምሽት አካባቢያቸውን ማህበራዊ ፍርድቤት ሠራተኛ እማኝ አድርገው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Shashitu Niguse

'እንደምን አደራችሁ? እንዴት ናችሁ?' ከሚል ጉርብትና ውጪ ዝምድና የሌላቸው ወ/ሮ ሻሺቱና ወ/ሮ ምግብ፤ በቃል የተሰጣጡትን አደራ አክብረው ዛሬ ይገናኛሉ።

የተወሰነ እቃ ደግሞ ለጎረቤታቸው እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፤ ስለዚህ እንደቃላቸው አደረጉ። የቀረው ቤት ነው። ቤታቸው ከጭቃ የተሰራ ሲሆን ያረፈው ደግሞ 200 ካሬ ሜትር በሚሆን መሬት ላይ መሆኑን ይናገራሉ።

በዘመኑ አጠራር አሞራ ክንፍ በሚባል ቅርጽ የተሰራው ይህ ቤት ሌሎች የሚከራዩ ሁለት ሰርቪስ ክፍሎችም በግቢው ውስጥ አሉ።

ወ/ሮ ሻሺቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የቤት ኪራይ ገንዘብ እየሰበሰቡ አስቀምጠውላቸዋል። በርግጥ የቤት ኪራይ ቤቱ በሚገኝበት ደብረብርሃን ሥላሴ ውድ አይደለም። ቢሆንም የወር ኪራዩን ተቀብለው በባንክ በማስቀመጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኘው ልጃቸው፣ በአንድ ወቅት እርሳቸውም በመጡበት ወቅት ለእርሳቸው መስጠታቸውን ይናገራሉ።

ይህንንም ወ/ሮ ምግብ እንደሚያስታውሱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት አረጋግጠዋል።

ቤቱን በሚመለከት የሚደረገውን መዋጮ፣ ዓመታዊ ግብር ከፍለው፣ ወ/ሮ ሻሺቱ ተመዝግበው የሄዱትን ውሃ አስገብተው እንዳቆይዋቸው ይናገራሉ።

በየጊዜው ከሰጧቸው የኪራይ ገንዘብ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት ከ50 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር በባንክ ማስቀመጣቸውን ወ/ሮ ሻሺቱ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ምግብ አንድ ጊዜ መጥተው ቤታቸውን አይተዋል። ቤታቸውን ትተው ሲሄዱ ተመልሼ አገኘው ይሆናል ብለው ያስቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። ለቃላቸው ታማኝ የሆኑት፣ ቃላቸውን ጠብቀው ያቆዩት ወ/ሮ ሻሺቱ የወ/ሮ ምግብን ተስፋ አሳክተዋል።

ከዚህ በፊት በመጡበት ወቅትም ቤታቸውና በህይወት የቆዩትን ጎረቤቶቸቸውን ሲያገኙ የነበረውንም ደስታ አይረሱትም።

ቤታቸው ሳይሸጥ አደራቸውን ጠብቀው በማቆየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ወደር እንደሌለው ይናገራሉ።

"በጨለማ የሰጡኝን በብርሃን እንዳስረክብ ፈጣረዬን እለምን ነበር" ይላሉ አደራ ጠባቂዋ ወ/ሮ ሻሺቱ።

ወ/ሮ ምግብም ቤታቸውን ተረክበው የዘመመውን አቅንተው ለመኖር እንደሚያስቡ ይናገራሉ። ልጆቻቸውም የተወለዱበት ቤት እናታቸው ለመኖር ማሰባቸውን ሲሰሙ ሃሳባቸውን መደገፉ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ሻሺቱ ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ ቤታቸውን እንዲጠብቅ ውክልና ለሰጡት ሰው የጎረቤታቸውን የወ/ሮ ምግብ ቤትም አደራ ብለው ውክልና ሰጥተው መሄዳቸውን ያስታውሳሉ።

በአደራ የተሰጠኝን ቤት ሳየው እንደራሴ ቤት ነው የሚሰማኝ የሚሉት ወ/ሮ ሻሼ ይህንን በአደራ የተሰጣቸውን ቤት ሲጠብቁ በርካታ ውጣ ውረዶች ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።

ከተከራይ ጋር መነጋገር፣ አጥር ፈርሶ ቢናገሩ፣ ግቢያቸው ተከብሮ እንዲቆይ በማድረግ ውስጥ ክፉ የሚናገር የአካባቢ ሰው አይጠፋም ነበር።

ሁለቱ ግለሰቦች ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት አንዳቸው ሚኒሶታ ሌላኛቸው ዳላስ ቢሆኑም ያሉበት ድረስ በመሄድ መጠያየቃቸውን አጫውተውናል።

ወ/ሮ ሻሺቲ ከ20 ዓመታት በላይ በአደራ ጠብቀው ያቆዩትን ቤት ለባለቤቷ ወ/ሮ ምግብ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ የካቲት 10/2010 ዓ.ም እዚያው ጎንደር ውስጥ እንደሚያስረክቡ ተናገረዋል።