አዲሱ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፈንታ በሹመታቸው ዙሪያ ምን ይላሉ?

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media Agency FB

ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ፣ በአማራ ብሔራዊ ክልልም የምሁራን መማክርት ጉባኤ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራርና አስተዳደር፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በቀጠናዊና አካባቢያዊ ልማት ጥናት (ሪጂናል ኤንድ ሎካል ዴቨሎፕመንት ስተዲስ) ዘርፍ አግኝተዋል። ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም በልማት ጥናት (ዴቨሎፕመንት ስተዲስ) ኔዘርላንድስ ዘሄግ ከሚገኘው ኢንስቲትዩት ኦፍ ሶሻል ስተዲስ ማግኘታቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ገልፀዋል።

ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የአማራ ክልል ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል። ቢቢሲ ትናንት አመሻሹን ደውሎ ለዶ/ር ፈንታ የተወሰኑ ጥያቄዎች አቅርቧል።

ምን አስተዋፅኦ አደርጋለሁ ብለው ነው ሹመቱን የተቀበሉት?

ዶ/ር ፈንታ፡ ብዙ ነገር አበረክታለሁ ብዬ አስባለሁ። እንደገና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ለግማሽ ክፍለ ዘመን የሚሆን የኢትዮጵያ ገበሬ ከኪሱ፣ እናቶች ከመቀነታቸው ፈተው ያስተማሩት ኢንተሌክችዋል [ምሁር] ቡድን ተገልሎ ቆይቷል፤ በገጠመው የታሪክ አጋጣሚ ምክንያት። በመሆኑም ጉዟችን አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አዳጋች እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ እኔ በግሌ ከእንግዲህ በኋላ ከውጪ በመሆን፣ ፖለቲካውን በመተቸት የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ማስተካከል አይቻልም [ብዬ አምናለሁ]። ገብቶ የምንችለውን ሁሉ፣ ፖለቲከኞችንም በማገዝ መለወጥ ይቻላል የሚል ትልቅ እምነት አለኝ።

ሙያዬ ሕዝብ አስተዳደርና ልማትና አመራር ነው። ከመጀመሪያ ጀምሮ በሕዝብ አስተዳደር ነው የተመረቅኩት። ሁለተኛ ዲግሪየዬን የጨረስኩት በአካባቢና ክልላዊ ልማት (ሪጂናል ኤንድ ሎካል ዴቬሎፕመንት ስተዲስ) ነው። ሦስተኛ ዲግሪዬ ልማት ጥናት (ዴቬሎፕመንት ስተዲስ) ነው። በመሰረታዊነት ደግሞ ዴቬሎፕመንት ስተዲስ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ነው። ስለዚህ የምርምር ጽሑፎቼ፣ የማስተማር ሥራዬ፣ አጠቃላይ ሕይወት ዘመኔ ከሕዝብ አስተዳደር ጋር ቁርኝት ያለው በመሆኑ እጅግ አስተዋጽኦ ማድረግ እችላለሁ ብዬ እገምታለሁ። ግምት ብቻ ሳይሆን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደምችል እምነት አለኝ።

ፖለቲከኛ መሆንና በተማሩበት ዘርፍ ማገልገል [academician] መሆን ይለያያል ለሚሉ ሰዎች ምን አስተያየት አለዎት?

ዶ/ር ፈንታ፡ እኔ የመጣሁት በተማርኩበት ሙያ ለማገልገል ነው። ዝም ብሎ የፖለቲካ ፖዚሽን [ሥልጣን] ለመውሰድ አይደለም። በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ በሚደረገው የሕዝብ አገልግሎትም መሰረታዊ የፖለቲካ እንቅፋቶቻችንና ድክመቶቻችን ወደኋላ መለስ ብለን በምናይበት ጊዜ የሕዝብ የአገልግሎት እርካታ ማነስ [አንዱ] ነው። መሠረታዊ ችግራቸው ይህ ነው። ይህንን ለማገዝ ደግሞ ፖለቲከኞች ብቻቸውን አይደለም። በዚህ ሙያ ላይ የተማሩ ሰዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ብቻ ሳይሆን ያበረክታሉ።

ሌላኛው ፖለቲከኛነትና አካዳሚሺያን መሆን [ምሁርነት] በፖዚሽን [በሥልጣን] የተለያየ ነው። አካዳሚክስ ፖለቲካን አያውቁም ማለት ግን አይደለም።

እኔ በመጀመሪያ ዲግሪዬ ማይነሬ ፖለቲካል ሳይንስ ነው፤ ይህንን ጠንቅቄ አውቃለሁ። ፖለቲከኛ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲካ ራሱ ምንድን ነው? የሚሉትን ጠንቅቄ አውቃለሁ። አንድ ይኼ ነው። ሁለተኛ እኔንና መሠሎቼ ያደግነው በዚህ ማህበረሰብ ውስብስብ በሆነ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ነው። ስለዚህ የየቀን ኑሯችን፣ የዕለት ተዕለት ኑሯችን፣ የፖለቲካ ኃላፊነት መውሰድና አለመውሰድ ካልሆነ በስተቀር ልዩነቱ፣ እያንዳንዱ ሰው፣ እንኳን እኔ በሙያው ቅርብ የሆንኩትና ያለፍኩበት ሰው ይቅርና ከሙያውም ሩቅ የሆነ ሰው ስለ ፖለቲካ የራሱ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን አቋም አለው። ስለዚህ ወደፊትም መታረም ያለበት ኢንቴሌክችዋልን ቴክኖክራት አድርጎ ብቻ መሳል ተገቢ አይደለም። የሕዝብን ፍላጎት ለማርካት ነው እዚያ ያሉት። የሕዝብን ፍላጎት ለማርካት ደግሞ አንዱ ትልቅ ጎዳና እንዲህ አይነትን አገልግሎት መስጠት ነው።

ስለዚህ እኔ አሁን አንድ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲሁ ወሰድኩ ብዬ ሳይሆን ሕዝብን በሰፊው ላገለግልበት ከምችልባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ትልቁ አጋጣሚ ነው የሚል የግል እምነት ነው ያለኝ። ስለዚህ ፖለቲካውን ምሁራን አያውቁም ብለው የሚደመድሙ ሰዎች ካሉ እኔ ትክክል አይደለም ብዬ ነው የማምነው። በብዙ አገሮችም ቢሆን የፖለቲካ ፖዚሽን [ሥልጣን] አያውቁም እንጂ ፖለቲካው የሚመራው በምሁራን ነው። ስለዚህ እምነቴ ይህ ነው። እርግጠኛ ነኝ የፖለቲካ ግንዛቤየም በቂ ነው። ከሕዝብ ጋር ኖረናል። የሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ጠንቅቀን እናውቃለን። የፖለቲካ አመራሩ ደግሞ በእንዲህ አይነት ቢታገዝ የበለጠ ውጤታማ፣ አሁን ካለንበት ደግሞ ወደፊት ለመራመድ ይጠቅማል ብዬ ነው የማምነው።

የተካሄደውን ሹም ሽር በተመለከተ የምክርቤት አባላት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል ሹመቱ (ከክልል ተነስተው ወደ ፌደራል የሄዱ) "ክልሉን ለማዳከም የተሠራ ነው፤ ጊዜውን የጠበቀም አይደለም" የሚሉት ይገኙበታል። እዚህ ላይ የግል አስተያየትዎ ምንድን ነው?በርግጥ የሚያሰጋ ነገር አለ?

ዶ/ር ፈንታ፡ እኔ የሚያሰጋ ነገር አይታየኝም። እነዚያ ወንድሞቻችን ወደ ፌደራል ኃላፊነት የሄዱት በዚህ ክልል ተወልደው፣ በዚህ ክልል ሕዝብ ውስጥ ያገለገሉ ናቸው። አሁንም ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ ሄዱ ማለት የዚህን ክልል ፖለቲካ ጭራሹኑ ዘንግተው ጥለውት ሄዱ ማለት አይደለም። የክልሉ ፖለቲካ በማዕከላዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ውክልና እንዲኖረው፣ የክልሉ መሠረታዊ የሆኑ ጥቅሞች በማዕከላዊ ደረጃ፣ የፖለቲካ ጥቅሞች፣ የኢኮኖሚ ጥቅሞች፣ የማህበራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ የሚያደርጉ ናቸው።

እኛ ደግሞ ከእነዚህ ሰዎች ጋራ በተለያየ የቴክኖክራት ወይንም ደግሞ የሙያ አገልግሎት ስንደግፍ እንዲሁ ዛሬ ከሰማይ የተወለድን ወይንም ዱብ ያልን ሰዎች አይደለንም። በመሰረቱ የሌሎቹ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለት ሰው እኮ ነው አዲስ የመጣው። እኔና ዶ/ር ሰዒድ ነን። ዶ/ር ሙሉነሽ የቢሮ ኃላፊ ሆና ያገለገለች ናት። ሁለት ሰው መጣና ያኛው እንዲህ ሆነ የሚለው ነገር እኔ እንደግል ብዙም አይታየኝም።

ከአማራ ክልል ተነስተው ፌደራል ስለሄዱ የፖለቲካ ሥርዓቱን ይዘነጋሉ የሚለውን ብዙም አልጋራም። "ሴራ ነው" የሚሉ ግለሰቦች የራሳቸው መብት ነው። ወደ ፖለቲካ ዓለም ስትመጪ ልትማሪ የሚገባው ትልቅ ነገር ግለሰቦች የሚመስላቸውን ሃሳብ ያራምዳሉ። ብዙኃኑን የገዛው ወደፊት ይኼዳል ማለት ነው። ዛሬም የሆነው ይህ ነው።

ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎችን ከመጥፎነት፣ ከተለያየ ችግር ነው ብዬ አልፈርጅም። እንደውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደፊት እንዲራመድ ከተፈለገ ከፍረጃ መውጣት መቻል አለብን። እያንዳንዱ ሃሳብ በራሱ ሜሪት [ባለው ዋጋ] ቆሞ መሄድ አለበት። ለሕዝቡ ወይንም ደግሞ ውሳኔ ለሚሰጠው አካል እንደዛሬው የምክር ቤት አባላት የጉዳዩን ምንነት ቁልጭ አድርጎ በማውጣት ብዙኃኑ የሚገዙት አድርጎ ነው መሸጥ ያለብን እንጂ እንዲሁ ገና ከመጀመሪያው ላይ የሆነ ነገር ለጥፈንለት ይኼ ነው ካልን [አስቸጋሪ ነው]። አንዱ ፖለቲካችን ወደፊት እንዳይንቀሳቀስ ቸንክሮ የያዘው ችግር ፍረጃ ነው።

ይህ የግል ሃሳቤ ነው። ሰዎቹን ግን አፕሪሺየት የማደርገው [የማደንቀው] ፣ ያመኑበትን ነገር በቀጥታ፣ በግልጽ ማንፀባረቃቸውን ነው። መለመድ ያለበትም፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ልትራመድ የምትችለውም እንዲህ ዓይነት ሀሳቦችን አንሸራሽሮ በመጨረሻ ላይ ሕዝብ ያመነበትን ወይንም የሕዝብ ወኪሎች ያመኑበትን ሲያሳልፉት ነው። ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለምናደርገው ጉዞም ራሱን የቻለ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ።

በክልሉ ሕዝብ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። በግልዎ ሕዝቡን ለማገልገል ምን ላይ ትኩረት ለማድረግ አስበዋል?

ዶ/ር ፈንታ፡ እንዳልሽው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። የዚህ ክልል፣ የሕዝቡ ትልቁ ጥያቄ መጀመሪያ የሚፈታው ጥያቄዎቹን ጊዜ ሰጥቶ በሰከነ፣ በተናበበ፣ በተረጋጋ መንፈስ፣ አገራዊ አንድነታችንን አባቶቻችን ዋጋ የከፈሉባትን አገር ሊያስቀጥል በሚችል፣ የአማራ ሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር ፖለቲካ ለመሥራት መደማመጥ ያስፈልጋል። መስከን ያስፈልጋል። ስለዚህ እነዚህ በሰከነ መንፈስ ጊዜ ወስደን የምንፈታቸው ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ለጠየቅሽኝ ጥያቄ በአስቸኳይ መጀመር አለበት ብዬ የማምነው የአማራ ሕዝብ የሕዝብ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እንዲዳረሰው ከማድረግ ነው።

በፍርድ ቤቶች ዜጎች ሄደው ያለመጉላላት፣ በጤና ተቋማት ሄደው ያለመጉላላት፣ ባለን ሀብት ሙሉ ጊዜያችንን መስዋዕት አድርገን ለዜጎች ጥቅምና ፍላጎት የሚቆጭ የመንግሥት ሠራተኛ እንዲኖር ማገዝና ማበረታታት፣ አብሮ መሥራት [እንዲሁም] አርዓያ ሆኖ ማሳየት የሚሉት ለኔ የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ምክንያቱም ለዜጎች ባለን አቅም፣ ባለን ሃብት አገልግሎት ከሰጠናቸው ሌሎቹን በመደማመጥ ወደፊት መሄድ እንችላለን።

ስለዚህ የእኔ የመጀመሪያ ትልቁ ሥራዬ የሚሆነው ሲቪል ሰርቪሱ ወይንም የመንግሥት ሠራተኛው በራሳችን ብዙ የምንለውጠው ነገር እንዳለ አምነን እንድንሠራ ጉልበት መሆን፣ ማበረታታት፣ ማነቃቃት ለሕዝባችን የማናደርገው ነገር ሊኖር እንደማይገባ፣ ሌሎች የምንጠይቃቸውን ጥያቄዎች እኛ በአቅማችን በእጃችን ውስጥ ያለውን ነገር አሟጠን ተጠቅመን ከዚያ በኋላ ይህ ይገባናል ብለን እንድንጠይቅ የሚያስችል አስተሳሰብና ሥነ ልቦና እንዲኖረን ማድረግ ነው።

ሕዝቡ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል በቅርቡ በሰላማዊ ሰልፍም ሲጠይቅ የነበረው እና የታገቱ ተማሪዎችን የተመለከተው ጉዳይ ነው። እርሱን በተመለከተ ለመሥራት ያሰቡት አለ?

ዶ/ር ፈንታ፡ ዛሬ እዚህ ቦታ ላይ ስለመጣሁ ሳይሆን ቀድሜ በነበርኩበትም ቦታ ላይ፣ በመማክርት ጉባኤም ሆነን ይህ ጉዳይ እጅግ የሚያሳስብ፣ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄም ነው መሆን ያለበት። ምክንያቱም የታገቱ ልጆች የአማራ ልጆች ስለሆኑ ብቻ ሌላው ተኝቶ የሚያድርበት አገር ከተፈጠረ ለነገ ምንም ዓይነት ዋስትና ሊኖረን ስለማይችል።

ነገር ግን ለዚህ ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋራ የማይቋረጥ፣ ያላሰለሰ፣ ቀጣይነት ያለው፣ ድምዳሜው የሚታወቅበትና የሚቋጭበት ሥራ ወጥ በሆነ መንገድ ሠርቶ፣ እየተሰቃዩ ላሉ ቤተሰቦቻቸውና ለሕዝቡም ባጠቃላይ ምላሽ መሰጠት መቻል አለበት። ምላሽ የሚሰጥበትን ስርዓት እንዲሁ በሚዲያ ላይ ወጥቶ በመናገር ሳይሆን ያላሰለሰ ሥራ መሥራትና ይህንን ጉዳይ መቋጨት አለበት።

የታገቱት ወገኖቻችን ማንኛውም ሥራ ተሰርቶ ወደቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉበትና ሁኔታዎቹ በግልጽ የሚታወቁበትን ሂደት ማወቅ፣ ምክንያቱም ከእንግዲህ በኋላ እንዲሁ ዝም ብለን ብንቀጥል እያንዳንዳችን መረዳት ያለብን ከታገቱት ውስጥ የእኔ ልጅ ብትሆን፣ የኔ እህት ብትሆን፣ የኔ ወንድም ቢሆን ብሎ ነው ሁሉም ማሰብ ያለበት። በሃገር መሪም ደረጃ ያሉ በክልልም አመራር ደረጃ ያለው፣ እያንዳንዱ ዜጋ ማሰብ ያለበት በዚህ ደረጃ ነው ብዬ ነው የማምነው። ይኼ ሥራ ይሰራል። ለዚህ ስራ እንዲሰራ ደግሞ የበኩሌን ያላሰለሰ ጥረት አደርጋለሁ ብዬ አምናለሁ።

ምን ተግዳሮት ይገጥመኛል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ፈንታ፡ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ይቅርና፣ በማንኛውም የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታቸው የተረጋጋ በሆኑ አገሮችም ቢሆን አዲስ ቢሮ ስትመጪ የተለያየ ኃሳቦች አሉ። እነዚያን ሀሳቦች እንደ ፎቶ ኮፒ ማሽን ኮፒ እያደረግሽ የምትልኪበት አይደለም። ሀሳብሽን ለመሸጥ ጊዜ ይጠይቃል። ሀሳብሽን አሳምነሽ ሌሎቹ ገዝተውት፣ ገበያ ላይ እንዲያውሉት ለማድረግ ጊዜ ይጠይቃል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ደግሞ እንደሚታየው ራሱን የቻለ ፈተና ስለገጠመው እነዚህን ነገሮች በቀላሉ ነገ ጠዋት ሸጬ ዋጋ አውጥተው አገኛለሁ የሚለው ፈታኝ ነው። እነዚህን ሀሳቦች ለሕዝብ፣ ለመንግሥት ሠራተኛው፣ ለፖለቲካ ኃላፊዎች፣ በበቂ ሁኔታ ማስረጽ ጊዜ ይወስዳል። እነዚህን ሥራዎች በመጣደፍ ሳይሆን በተረጋጋ ሥራ ካልሠራናቸው ራሳቸውን የቻሉ ፈተናዎችም ይሆናሉ።

ይኼ ካልሆነ፤ በአንድ ምሽት ብለሽ የምታስቢ ከሆነ ምናልባትም ከስበት ተቃራኒ የሚሄድ ይሆናል። በቃ የሚቀበል ሕዝብ የለም፣ የሚቀበል አመራር የለም፣ ብለን ቶሎ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሥነ ልቦና ዝግጅት ስላለኝ ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችም በዚህ መንገድ እንወጣለን ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው።