ከማዕከላዊ ስልጣን የተገፋው ህወሓት ከዬት ወደዬት?

የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና መለስ ዜናዊ

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages/TONY KARUMBA

ከሰሞኑ ህወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበት 45ኛ አመት ክብረ በዓል በትግራይ በደማቅ ሁኔታ በመከበር ላይ ነው።

የደርግን ስርአት ገርስሶ ስልጣን ከተቆጣጠረ ከሶስት አስርት አመታት በኋላ ከማዕከላዊ መንግሥት ስልጣንም ገሸሽ ተደርጎ ክልሉን እያስተዳደረ ይገኛል። ለመሆኑ ህወሓት ከዬት ተነስቶ የት ደረሰ? በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ያደረጋቸው አስተዋፅኦዎች ምን ይመስላሉ? ስህተቶቹስ ምን ይመስላሉ? በጨረፍታ እንመለከተዋለን።

ደደቢት፣ የህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ፣ የደርግን ጭቆና የተፀየፉና ነፃነትን የናፈቁ ወጣቶች፣ የብዙ ወጣቶች ደም የተገበረባት ቦታ።

የነገን ተስፋ የሰነቁባት ወጣቶች የደርግን ስርአት ለመገርሰስ ተነሱ፤ ትግሉም እልህ አስጨራሽና ብዙዎችም የተሰውበት ነው።

በድርጅቱ የተለያዩ ሰነዶችም ሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚነገረው የትግሉ ዋና ዓላማ የልማትና የዴሞክራሲ ዕንቅፋት ሆኗል ብሎ ያመነውን የደርግ ስርዓት አስወግዶ ወደ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ለመሸጋገር ነበር።

ከአስራ ሰባት አመታት ትግል በኋላ የደርግ ስርአትም ተገረሰሰ፣ ህወሓት ከብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ኢህዴንና ሌሎች አጋር ፓርቲዎች ጋር በመሆን ስልጣን ተቆናጠጠ።

የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ለሶስት አመታት ያህልም ቆይቷል፤ በዚህ ወቅት ነው አገሪቱ አዲስ ህገ መንግሥት እንዲኖራትና ፌደራላዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ የሚል መጠሪያ እንዲኖራትም የተወሰነው።

ህወሓትና ህገመንግሥቱ

ህዳር 29፣ 1987 ዓ.ም በወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ተፈርሞ የፀደቀው ህገ መንግሥት ለብሄር ብሄረሰቦች የተለየ መብት የሚሰጥ እንዲሁም በመርህ ደረጃ ለህዝቡ የስልጣን ባለቤትነትን የሚያጎናጽፍ ነው።

ህገ መንግሥቱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ፤ የዜጎች የመጻፍ፣ በነጻነት ሃሳብ የመግለጽ፣ የመሰባሰብና የመቃወም መብቶችን አካቶ የያዘ ሰነድ በመሆኑ ድጋፍ ተችሮት ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ህገ መንግሥቱንም በማርቀቅ የተለያዩ ሃሳብ ያላቸውን ኃይሎችንም በማሰባሰቡ ህገ መንግሥቱ በመርህ ደረጃ ብዙዎች ደግፈውታል።

ምንም እንኳን ህገ መንግሥቱ ከተለያዩ ሃይሎች ድጋፍ ቢቸረውም አንዳንድ አንቀፆች አሁንም ድረስ ያልተቋጨ ውዝግብን አስነስተዋል። ለምሳሌም ያህል አንቀፅ 39 ላይ የሰፈረው 'ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ድረስ' የሚለው ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሃገር ሆና እንዳትቀጥል ህልውናዋን የሚገዳዳራት ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ እስካሁን ላሉ የብሄር ጥያቄዎችን ራሳቸውን የማስተዳደር ታሪካዊ ጥያቄ የመለሰ ነው የሚሉም በሌላ ወገን አልታጡም።

በህወሓት/ኢህአዴግ ፊት አውራሪነት የጸደቀው አዲሱ ሕገ መንግስት፤ ከዚህ በፊት የነበረውን በአሃዳዊነት ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ አገር ግንባታ አፍርሶ ሌላ መልክ የሰጠ ነው ተብሎ ይተቻልም እንዲሁም በተቃራኒው ይሞካሻል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ሲከታተሉ ለቆዩት የግጭት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሼትል ትሮንቮ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ የሚያንጸባርቅና በአብዛኛው የህዝቡ ስሜት የሚገልጽ እንደነበር ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የኢህአዴግ ስርዓት ትልቁ ችግር ራሱ ህገ-መንግስቱ ሳይሆን፤ አተገባበር ላይ የነበሩ ክፍተቶችና ጉድለቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages/JOSE CENDON

ምርጫ 1997፡ የሞክራሲተስፋ መፈንጠቅ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የ1997 ምርጫ እንደ ትልቅ ምዕራፍ ይታያል። በነበሩት የጦፉ ውይይቶችና መድረኮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው በአንድ ግንባር መምጣት፣ በምርጫ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ህዝቡ ይሆነኛል የሚለውን የመምረጥ ተስፋን ያመጣ ነበር።

ከዛ በፊት በነበረው የመጀመሪያው ምርጫ ከጠቅላላ 547 የፓርላማ ወንበሮች ውስጥ ኢህአዴግ 481 አሸንፎ ነበር ስልጣኑን ከሽግግር መንግስቱ የተረከበው።

በወቅቱ እነ ዶክተር መረራ ጉዲና የመሳሰሉ ነባር የተቃዋሚ አመራሮች ጥቂት መቀመጫ አግኝተው በምክር ቤቱ የተለዬ ሃሳባቸውን ለመግለጽ ዕድል አግኝተው ነበር።

የተሻለ የዲሞክራሲ ጭላንጭል የታየበት የ1997ቱ ምርጫም፤ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ፅሁፎች ነበሩባቸው ተብለው ቢተቹም፤ የግል ሚድያዎችና ሲቪክ ማህበረሰቦች እንደልባቸው የተንቀሳቀሱበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።

በተለይም የተቃዋሚዎች ተጣምረው አንድ ላይ መምጣት ለምርጫው ሌላ መልክ ነበር።

በወቅቱ ቅንጅትና ህብረት ኢህአዴግን ተገዳድረውታል፤ ተንታኞች እንደሚሉት ኢህአዴግ ባልጠበቀው መልኩ የሃገሪቱን ማዕከል አዲስአበባን በተቃዋሚዎች አጥቷል።

ሆኖም በምርጫው ውጤት ተቃዋሚዎችና ኢህአዴግ ስለልተስማሙ ወደ እስርና ደም መፋሰስ ነበር ያመራው።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች ህገመንግሥቱን በኃይል ለማፍረስና በሃገር ክህደት ተወንጅለው ዘብጥያ ወረዱ። ምንም እንኳን ብዙዎቹ ከመንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ከእስር ቢፈቱም በርካቶች በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ስለቆረጡ ስደትን ምርጫ ለማድረግ ተገደዱ።

ብዙዎቹ በውጭ ሆነው ሲታገሉ ቆይተው ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የተደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ ነበር ወደ አገር ቤት የመጡት።

በ1997 ምርጫ ስልጣኑ ለመጀመርያ ግዜ የተነቃነቀው ገዢው ፓርቲ ከፍቶት የነበረውን ጭላንጭልም ተዘጋ፤ ይህንንም የሚያጠናክርና በተቋማዊ መልኩ የሚያደርጉ ህጎች ፀደቁ።

ከነዚህም መካከል በብዙዎች ዘንድ አፋኝ ተብለው የሚጠሩት የጸረ ሽብር፣ የፕሬስ፣ የሲቪል ማህበረሰብ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምዘገባ አዋጆች ይገኙበታል። ብዙዎችንም በፍርሃት እንዲሸበቡ አድርጓቸዋል፤ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበውታል በማለት በተደጋጋሚ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሪፖርቶችንም ያወጡ ነበር።

የቀድሞ የህወሓት አመራር አባል አቶ ገብሩ አስራትም አስተያየት ከዚህ ብዙ የተለየ አይደለም፤ በወቅቱ ገዢው ፓርቲ የወሰደውን እርምጃ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ዕድገት ወደኋላ የጎተተ ክስተት ይሉታል።

ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችንም ከማሽመድመድ ሌላ የምርጫ ውዝግቡን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ አዳዲስ አባላትን መመልመል ጀመረ። ከምርጫ 1997 በፊት ከአንድ ሚልዮን በላይ አባላት ያልነበሩት ቢሆንም የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ 7 ሚሊዮን አዳዲስ አባላትን መልምሏል።

በሚሊዮኖች የተመለመሉት አባላት የኢህአዴግን ርዕዮተ አለም፣ ፕሮግራም እንዲሁም ለሃገሪቱ አስቀመጥኩት የሚለውን አቅጣጫ አምነውበት ሳይሆን፣ ከመንግሥታዊ ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዙ እንደሆኑም በቅርበት ግንባሩን የሚከታተሉ በተደጋጋሚ ይናገሩት የነበረ ጉዳይ ነው።

ግንባሩን ሳያምኑበት በአባልነት የተመለመሉ ወጣቶች በመጨረሻ ድርጅቱ አደጋ እንደሚያስከትል ስጋታቸውን የገለጹም ብዙዎች ነበሩ፤ ግንባሩም መሸርሸሩ አይቀርም በማለትም ተንታኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"የተራበው ህዝብ መሪውን ይበላል" በሚልና በሌላ መረር ያሉ ንግግሮቻቸው የሚታወሱት መረራ ጉዲና (ዶ/ር) "የኢህአዴግ መጨረሻው ከአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ ሊሆን ይችላል በሚለው እንጂ በህዝባዊ ዓመጽ እንደሚሆን አውቅ ነበር" ይላሉ ከቢቢሲ ጋር በባደረጉት ቆይታ።

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages/AFP

ነጻ የሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ክፍተት?

ኢትዮጵያ ውስጥ እምነት የሚጣልበት የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አለመኖር እንደ አንድ ለስርአቱ ችግር ተብለው ከሚነሱ ምክንያቶች አንዱ ነው።

ምንም እንኳን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ አንዱ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ምሰሶ የሆነው የተቋማት እርስ በርስ የመቆጣጠር እና ሚዛን መጠበቅ ቢሆንም አገራዊ እና መንግሥታዊ መዋቅሮች ከኢህአዴግ ነፃ አልነበሩም። ለዘመናትም መንግሥታዊና የህዝብ ተቋማት የፓርቲው መሳሪያ ሆነው ከፍተኛ ክፍተትን አስከትለዋልም ተብለው ይተቻሉ።

ለዚህም የፍትህ አካላት፣ የፀጥታና ደህንነት አካላት ኢህአዴግ እንደ ግል ንብረቱ የሚጠቀምባቸውና የሚያሽከረክራቸው ናቸው ይባላሉ።

ለምሳሌም ያህል የመንግሥት ሚዲያ ለአስርት አመታት ያህል የገዢው ፖርቲ ፕሮፓጋንዳ መንዢያ ናቸው ይላሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ ፍርድ ቤትም ሆነ አስፈፃሚው አካል ፓርቲው ጣልቃ እየገባ እንደፈለገ የሚያዛቸው ናቸው ይላሉ ተችዎች።

በተደጋጋሚ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ተጠርጣሪዎችን በመንግሥት ሚድያ እንደ ወንጀለኞች ተደርገው የተለያዩ ዘገባዎች የሚቀርቡባቸው አካሄድ ነበር፤ ይሄ ሁኔታ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ቀጥሏል። ፍርድ ቤቱም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ይህንን ሲያስቆምም አይታይም ይላሉ።

በባለፉት ሶስት አስርት አመታት ያሉትን ክፍተትም በመታዘብ በኢትዮጵያ የከፋው ነገር ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማት መፍጠር አለመቻል እንደሆነ ፕሮፌሰር ትሮንቮል ይናገራሉ።

"ገዢው ፓርቲ ራሱን ከመንግሥት ተቋማት ጋር አጣብቆ፤ ተቋማቱ ራሳቸውን ችለው እንዳይቆሙ አድርጓቸዋል"ይላሉ።

ፕሮፌሰር ትሮንቮል እንደሚሉት ለዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት በሶስቱም የመንግሥት አካላት- ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው መካካል የእርስ በርስ ሚዛናቸውን ጠብቀው፣ ተለያይተውና አንዱ ሌላውን ሊቆጣጠር ስላልቻለ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, GettyImages/Sean Gallup

የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ- አብዮታዊ ዴሞክራሲ?

ምንም እንኳን የኢህአዴግ "አፋኝ እርምጃዎች፣ ፈላጭ ቆራጭ መሆን የጀመረው ምርጫ 97ን ተከትሎ፤ በውጤቱ ተደናግጦ ነው የሚሉ ቢኖሩም አቶ ገብሩ አስራት ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። ለሳቸው ዋነኛውና መሰረታዊው ችግር የግንባሩ ርዕዮተ ዓለም ነው።

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ከህገ መንግሥቱ ጋር ይጻረራል የሚሉት አቶ ገብሩ " ስርዓቱ ሁሉንም ዜጎች እኩል አይመለከትም፤ ወዳጅና ጠላት ብሎ ዜጎችን ለሁለት ይከፍላል" ይላሉ።

እንደ ማስረጃነት ድርጅቱ ይጠቅሳቸው ከነበሩትም መካከል "ለሰራተኞችና ለአርሶ አደር እቆማለሁ ይላል። ምሁር ወላዋይ ነው ብሎ ያምናል።" በማለት ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ይህ አስተሳሰብ ለህወሓትም ሆነ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግል ወቅት ህዝቡን ለማንቀሳቀስ ጠቃሚ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ ሆኖም ትግሉ ተጠናቆ ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ የተቀመጠ አቅጣጫ እንደሌለ ይጠቁማሉ።

"እንዴት እንቀጥልበት የሚለው ላይ አልተነጋገርንም" ይላሉ

አብዮታዊ ዴሞክራሲ በአቶ ገብሩ አስራት ብቻ ሳይሆን በብዙ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኞችና ምሁራንም ሲተች ይደመጣል፤ እንደ ርዕዮተ አለምም የማያዩት አሉ።

"ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም የሚመራና በፕሮግራሙ ላይ ለሰፈሩት ዓላማዎች የሚታገል ድርጅት ነው። ያነገባቸው ዓላማዎች ዴሞክራሲያዊና አብዮታዊ በመሆናቸው በተግባር ላይ ከዋሉ ኅብረተሰባችንን ከሚገኝበት ድህነትና ኋላ ቀርነት አላቀው ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና ያበቁታል። " ይላል ከኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ አንቀጽ ላይ የተወሰደው

ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርን መሰረት ያደረገው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለማስፈን የህዝብ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል የሚል ሲሆን፤ በጥቅሉ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ጠንካራ የመካከለኛ ገቢ ያለው መደብ መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚያስፈልገው ነውም ይላል።

ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው "የኢትየጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች፡ የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ" በሚለው ፅሁፋቸው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና መሰረት ስልጣን ላይ መምጫው መንገድ የማኦው ፍልስፍና የሆነው "ስልጣን የሚመጣው ከጠመንጃ አፈሙዝ ነው" የሚለው ነው ይላሉ።

አክለውም ይህንን የኢህአዴግ አስተሳሰብ ራሱ በህገ መንግስቱ ውስጥ ከገባው ቃል ይጻረራል ሲሉ ያስረዳሉ።

ጠንካራ ፖርቲ በመመስረት የሚያምነው ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን እንዲኖሩ የሚፈልገው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ሳይሆን ለይስሙላና ለለጋሾች ተብሎ እንደሆነም ትችቶች ከሚቀርቡባቸው ጉዳይ አንዱ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Gettyimages/ALEXANDER JOE

የልማታዊ መንግሥት ጥያቄ

ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የጤና አገልግሎት ሽፋን፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መንግሥት የሚያራምደው የልማታዊ መንግሥት ርዕዮት ውጤት ነው ብለው ብዙዎች ያምናሉ።

በተቃራኒው የዚሁ ልማታዊ መንግሥት መገለጫም የተለየ እይታዎችን የያዙ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች በእስር መማቀቅ ነው። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተቀረፀ የሚባለው የኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት መገለጫዎች የሚባሉት ጠንካራ እና ጣልቃ ገብነት ያለው፣ ለሰው ሐብት ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ የሀገርን ሐብትን በማስተባበር ቀጥተኛ ሚና በመጫወት ትልልቅ ሀገር አቀፍ የልማት ሥራዎችን ለመተግበር እንዲችል በማመቻቸት ለውጥ ማምጣት ነው ይላሉ።

ልማታዊ መንግሥቱ ያለ ሌሎች ተፅእኖ ራሱን የሚያስተዳድር እና በሃገር ውስጥ የበላይነት ያለው በምርጫ ሂደት የማይስተጓጎሉ ሲሆኑ የእስያ ሃገራቱ ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን እንደ አብነት ይጠቀሳሉ። ከምዕራባውያኑ ተቋማት አለም ባንክ እና አይኤምኤፍ "ያረጀ ያፈጀ" አካሄድ ነፃ በመሆን በፍጥነት እመርታዊ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ የሚልም አካሄድ ነበረው።

በዚህ አካሄድ ብዙ አስርት አመታትን በስልጣን የሚቆዩ ሃገራት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አምጥተዋል ቢባልም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ይደፈጥጣሉ ተብለው ይተቻሉ፤ ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን በማስገባት ይተቿታል።

የሲቪል ማሕበራትንና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ድምጽን በማፈን በተቃራኒ ወደ አምባ ገነንነትና ፈላጭ ቆራጭነት አምርተዋል ቢባልም ይህንን አስተሳሰብ ለዘመናት ኢህአዴግ በተለይ መለስ ዜናዊ ሲሞግቱት ነበር።

የመጡ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች

የመጡ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን በተመለከተ እንደ አለም ባንክ ያሉ መረጃዎች ሲፈተሹ በተከታታይ አመታት በዓለማችን ከፍተኛ ዕድገት ካሳዩ አገራት አንዷ ሆናለች፤ በአለም በፍጥነት በማደግ ላይ ከነበሩ አምስት ሀገራት መካከልም ሁና ነበር።

አዳዲስ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መጀመር ለምሳሌ የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ በርካታ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦች ተሰርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሴፍቲኔት መርሐ ግብር የሚጠቀስ ሲሆን በአለም ባንክ መረጃ መሰረት በጎርጎሳውያኑ በ2011፣ 30 % ህዝብ ከድህነት ወለል በታች የነበረ ሲሆን በ2016 ወደ 24% ቀንሷል። የትምህርት ቤት ተደራሽነትም እንዲሁ በ2006 97%፣ በ2016 ደግሞ ወደ 99% እንዳደገ መረጃው ያመለክታል።

ምንም እንኳን እነዚህ የመጡ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በተለያዩ አለም አቀፍ ሚድያዎች ከፍተኛ መወደስን ቢያመጡም መንግሥት ያደረጋቸውም ጫናዎችና ጭቆናዎች በብዙዎች ዘንድ ተተችቶበታል።

ስልጣን ላይ ለመቆየት የማያደርገው ነገር የለም የሚሉት ዶክተር መረራ በተለይም በ2002 በነበረው ምርጫ 99 በመቶ አሸነፍኩ ማለቱን እንደ ምሳሌ ያነሳሉ። ምክር ቤቱን ጠቅልሎ የሚቆጣጠርበት ዘዴም ያበጀ ሲሆን 'የምርጫ ሰራዊት' የሚባል ከእርዳታ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በማስተሳሰር አንድ ለአምስት "የሚጠረነፉበትን" ሁኔታም ተቀየሰ።

የምርጫው ውጤት ያልተቀበሉ ተቃዋሚዎችም እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ቢሄዱም ለውጥ ግን አላገኙም።

ቱ ፈላጭ ቆራጭነት

ከሰላሳ ዓመታት በላይ የህወሓት እና ኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆነው የቆዩት አቶ መለስ ዜናዊ በትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ባመጡት የኢኮኖሚ ለውጥ ጋር ተያይዞ ስማቸው ቢነሳም ባገሪቱ ውስጥ ግን በነበረው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓትም ይወቀሳሉ።

"ግንባሩ የመበስበስ አደጋ እንዳይገጥመው" በሚል ጀምረውት የነበረውን የመተካካት ፖሊሲም ከግብ ሳያደርሱ በ57 ዓመታቸው አረፉ።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአፍሪካ ተቀባይነት ያገኙ መሪዎች ውስጥ ቢካተቱም እንዲሁም "ባለ ራዕይ እንዲሁም ሞጋች ተደርገው ቢታዩም በሌላ መልኩ ዘኢኮኖሚስት መፅሄት ግን 'The man who tried to make dictatorship acceptable' (አምባገነንት ተቀባይነት እንዲያገኝ የሞከሩ ሰው) በማለት ይገልፃቸዋል።

ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ አገሪቱን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በቀደመው ራዕይ ቀጠሉበት፤ ፈላጭ ቆራጭነቱም ቀጥሎ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች መታሰር ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ነበር።

የህወሓት የቀድሞ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃነ ፅጋብ 'የኢህአዴግ ቁልቁለት ጉዞ' በሚለው መጽሐፋቸው ከመለስ ሞት በኋላ የግንባሩን አካሄድ የፈተሹት ሲሆን በሳቸውም አስተያየት

"በግምገማ፣ ራስን በመተቸት የሚታወቅ ፓርቲ በመተዛዘል (እከከኝ ልከክህ) ዳዴ ማለት ጀመረ፤ ሺዎች ደማቸውን የከፈሉበት ሥርዓት፣ የፓርቲው መሪዎች የግል ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበት ሆነ" በማለት ያስረዳሉ።

የኢህአዴግ የሥርዓት መበስበበስም መገለጫ የሆነው ሕዝባዊ ተቃውሞዎችና የሕዝቡ ቁጣ ናቸው።

በኢህአዴግ ላይ የሚንፀባረቁት ከፍተኛ ተቃውሞዎች በተለይም ግንባሩን በአካሉና በአምሳሉ ከሠራው ህወሓት ጋር በከፍተኛ ሁኔታ ያነጣጠረ ነው። ህወሓት ላይ የሚያጋጥሙ ማንኛውም እክሎች ግንባሩንም ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ነበራቸው። ለዚህም በህወሓት ያጋጠመው መከፋፈል በአገሪቱ ውስጥ ላለው መከላከያ እንዲሁም ሌሎች ተቋማትን የከፋፈለ እንዲሁም የአገሪቱን ደህንነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር።

ኢህአዴግ ወይም ህወሓትም ላይ ያነጣጠረው ተቃውሞም የትግራይ ሕዝብ ላይ የወረደ ሲሆን የትግራይ ሕዝብ በተለየ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ተደርጎም ተስሏል።

ይህ ሁኔታም ከራሱ ከፓርቲው ሲወጡ የነበሩ ሃሰተኛ ሪፖርቶችና ፕሮፖጋንዳዎች ሁኔታውን አባብሶታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፤ ይህንንም ሁኔታ ዶ/ር ደብረፅዮን ወደ ፓርቲው ኃላፊነት ሲመጡ ያመኑበት ጉዳይ ነው።

መቋጫ

በህወሓት አካሄድ ያልተደሰቱ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆነው አብርሃ ሃይለዝጊ አይነት ግለሰቦች ፓርቲውን ለቀው ለመውጣት ብዙ አልወሰደባቸውም። ለሶስት ዓመት የፓርቲው አባል የነበረ ሲሆን፤ ፓርቲውን ጥሎ ለመውጣት ግን አራት ዓመትም አልሞላም።

"ፓርቲው ከሕዝባዊነት ወጥቶ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው ሲያውሉት አስተዋልኩኝ። በፓርቲው ውስጥ ሆኜ ለመታገል የሚያስችል ቦታም እንዳልነበረም ተረዳሁ" በማለት ከፓርቲው ደብዳቤ በመፃፍ እንደተሰናበተ ያስታውሳል።

አብርሃ በፓርቲው ውስጥ ሆኖ ለመንቀፍ የሞከረ ሰው ከሥራ የመባረር፣ በሕይወቱ የማስፈራራት እና ሌሎችም ችግሮች ይደርሱበት ነበር ይላል።

"ጥያቄ የጠየቀ እንደ ጠላት ይታያል። ጠባብ፣ ትምክህተኛ የሚሉ የአፈና መሣርያ ቃላትን በመጠቀም ያሸማቅቃሉ" ይላል።

በወቅቱ ትክክለኛ ውሳኔ እንደወሰነ የሚሰማው አብርሃ በኋላም ህወሓት ባደረገው ጥልቅ ግምገማ ስህተት መሆኑ ታምኖበት ነበር ይላል።

ህወሓት በ2010 ዓ.ም ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጥልቅ ግምገማ ዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንደታፈነ፣ በፓርቲው ሥርዓት አልበኝነት እንደነገሰ፣ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አሠራር እና መጠቃቃት የፓርቲው መገለጫ እንደነበር በማመን ለሕዝብ ይቅርታ ጠይቋል።

ባለፉት 27 አመታት ድህነት፣ ሲፈፀም የነበረ ግፍ እና ሕገ-መንግስታዊ ጥሰት፣ የዜጎች ሰብኣዊ መብት ጥሰት በትግራይ የከፋ እንደነበርም ተንታኞች ይናገራሉ።

"ለረዥም ጊዜ በስልጣን የቆየ ገዢ ፓርቲ መጨረሻው ሙስና እና ሥርዓት አልበኝነት ነው" የሚሉት ፕሮፌሰር ሼቲል ትሮንቮል፤ ህወሓት እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ግንባር ከታገለበት መስመር ወጥቷል በማለት ሀሳቡን ያጠናቅቃል።

ዶክተር መረራም ስለ ህወሓት/ ኢህአዴግ የሚያስታውሱት ጥሩ ነገር ካለ ተጠይቀው "ከሰይጣኑ ደርግ ነፃ ስላወጣን ብቻ አመሰግነዋለው" ብለዋል።