በጀርመን በተፈጸመ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

የጀርመን ፖሊስ ጥቃቱ በደረሰበት ስፍራ ምርመራ እያደረገ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጀርመን የሺሻ ባር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስምንት ሰዎች መሞታቸውንና ጥቃት ፈጻሚዎቹ ማምለጠጣቸው ተነገረ።

መሣሪያ የታጠቁ ግለሰቦች ባደረሱት ጥቃት ከሞቱት ሰዎች ባሻገር ቢያንስ አምስት ሰዎች ሳይጎዱ እንዳልቀሩ የአካባቢው ፖሊስ ተናግሯል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት ስፍራ ሃናው የሚባል ሲሆን ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን እየፈለገ መሆኑን አስታውቋል።

ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ጥቃቱ የደረሰው በሁለት ስፍራዎች ሲሆን አንዱ በመሃል ከተማ ሌላኛው ደግሞ ከመሃል ከተማው ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው።

ፖሊስ በሁለቱም ስፍራዎች በሄሊኮፕተር በመታገዝ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ አሰሳ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ጥቃቱ የደረሰው እኩለ ለሊት ላይ ሲሆን ቁጥራቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች በሺሻ ባር ውስጥ የተቀመጡ ሦስት ሰዎች ከገደሉ በኋላ ወደ አሬና ባርና ካፌ በማምራት ሌሎች አምስት ሰዎችን መግደላቸው ተሰምቷል።

ጥቃቱን ያደረሱበት ምክንያት አልታወቀም ሲል ፖሊስ ገልጿል።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት በአካባቢው አባቱና ወንድሙ እንደነበሩ የተናገረው የኪዮስክ ሠራተኛ "ልክ እንደ ፊልም ነው። የሆነ የማይጥም ቀልድ ዓይነት ነገር፣ የሆነ ሰው ሊቀልድብን የመጣ ነበር የሚመስለው" ብሏል ለሮይተርስ የዜና ወኪል በሰጠው ቃል።

"በአጠቃላይ ምን እንደተከሰተ ገና አላብላላሁትም። አጠቃላይ የሥራ ባልደረቦቼ ቤተሰቦቼ እንደማለት ናቸው- እነርሱ እንኳ ምን አንደሆነ በውል አላወቁትም" ብሏል።

ጥቃቱ የተፈፀመባት ሃናኡ ግዛት ከምሥራቃዊ ፍራንክፈርት 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።

ከአራት ቀን በፊት በበርሊን ቱርኮች በሚበዙበት አካባቢ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው መሞቱ ይታወሳል።