የ 'ኮፒ ፔስት' ፈጣሪ ሞተ

ላሪ ተስለር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ላሪ ተስለር

ከት፣ ኮፒ፣ ፔስት፤ በርካቶቻችን እኒህን ሦስት ትዕዛዞች ለኮምፒውተራችን አስተላልፈን ጽሑፍን ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላው ቀድተናል፣ አላስፈላጊ ሀተታንም አስወግደናል።

ከት፣ ኮፒ እና ፔስት የሚሉትን ሦስት የኮምፒውተር ትዕዛዝ አይነቶች የፈጠረው ግለሰብ ላሪ ተስለር ይባላል። የኮምፒውተር ልሂቁ ላሪ በ74 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ላሪ በግዙፉ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሲልከን ቫሊ መሥራት የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1960ዎቹ መባቻ ነበር። ያኔ ኮምፒውተር ያላቸው ሰዎች እምብዛም አልነበሩም።

ላሪ የፈጠራቸው ኮፒ፣ ፔስት እና ከት የኮምፒውተር አጠቃቀምን አቅልለዋል፤ አዘምነዋልም።

'ፋይንድ ኤንድ ሪፕሌስ'ን ጨምሮ ሌሎችም አሠራሮችን የፈለሰፈው ላሪ፤ ቀድሞ ይሠራበት የነበረው ዜሮክስ በሞቱ ሀዘናቸውን ከገለጹ መካከል ይጠቀሳል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1945 ኒው ዮርክ ውስጥ የተወለደው ባለሙያው፤ የስታንፎርድ ምሩቅ ነው። ዋነኛ የፈጠራ ትኩረቱም ኮምፒውተርን ለተጠቃሚዎች ምቹ ማድረግ ነበር።

ላሪ በአፕል፣ በአማዞን፣ በያሁ እና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሠርቷል።

'ኮፒ ፔሰት'

ጽሑፍን ለመቁረጥ እንዲሁም ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ለማሻገር የሚውለው የከት፣ ኮፒ እና ፔስት ሀሳብ የተጠነሰሰው እንዲህ ነበር።

ቀድሞ ሰዎች ወረቀት ላይ ያሰፈሩትን ጽሑፍ ከአንድ አንቀጽ ወደ ሌላው ለማሻገር ወይም ቆርጠው ለማውጣት ሲፈልጉ ጽሑፉን ቀደው ማውጣት ነበረባቸው። ከኮፒ ፔስት መፈልሰፍ በኋላ ግን አርትኦት ዛሬ የሚገኝበትን ቅርጽ ይዟል።

ኮፒ፣ ፔስት እና ከት በአፕል ሶፍትዌር ላይ የተካተቱት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1983 ነበር።