የሰላም ስምምነት አዙሪት ውስጥ ያለችው ደቡብ ሱዳን

ሳልቫኪርና ሪክማቻር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻር የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በመስማማት የተፈራረሙት እኤአ በ2018 መስከረም ወር ላይ ነበር

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና የቀድሞ የአማፂያን መሪው ሪክ ማቻር የሽግግር የአንድነት መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት ከየካቲት 14 (ፌብርዋሪ 22) በፊት ነበር።

ማቻር የቀድሞ ሥልጣናቸውን፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ ለመያዝ የተስማሙ ሲሆን ለበርካታ ተቃማዊዎች ሥልጣን ለማጋራት በሚል በአሁን ሰዓት ያለው ካቢኔም ይበተናል።

እንደ ሥልጣን መጋራት ያሉና የአማፂያን ተዋጊዎችን ከመደበኛ ኃይሉ ጋር ማቀላቀል የሚሉ አንዳንድ ጉዳዮች ያልተፈቱ ሲሆን መንግሥት ለመመስረት እና ሌሎች ጉዳዮችን ከዚያ በኋላ ለመነጋገር ተስማምተዋል።

የቀድሞው የአማፂያን መሪ ሪክ ማቻር፣ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መሃላም ይፈፅማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስምምነቱ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱም ወገኖች ለሥልጣን በሚያደርጉት ትግል ወቅት ሆነ ብለው ሰላማዊ ዜጎች እንዲራቡ አድርገዋል የሚል ሪፖርት ካወጣ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

የሥምምነቱ ረብ እንዴት ያለ ነው?

ሥምምነቱ ስድስት ዓመት የዘለቀውንና ከ400 ሺህ በላይ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውና ከ12 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ያፈናቀለውን የደቡብ ሱዳናውያን እርስ በእርስ ጦርነት ያቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

ፕሬዝዳንት ኪር፣ ለሦስት ዓመት ያህል ይቆያል የተባለው የሽግግር መንግሥት በመመስረቱ ያላቸውን ተስፋ የገለፁ ሲሆን በዚህ ዓመት ውስጥም ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ወደመኖሪያ መንደራቸው ይመለሳሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በእርስ በእርስ ጦርነቱ ከሞቱትና ከተፈናቀሉት ዜጎች በተጨማሪ በርካታ ሰዎች እንዲራቡና እስካሁን ድረስ ላልተነገረ ስቃይ እንዲጋለጡ ተደርጓል።

ደቡብ ሱዳን ረዥም ዓመት ከወሰደው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ከሱዳን ተለይታ ራሷን የቻለች አገር የሆነችው እኤአ በ2011 ነው። ይህ ሠላም ያመጣል የተባለ ቢሆንም ሠላም ከደቡብ ሱዳናውያን እጅ እያፈተለከ መሄድ የጀመረው ወዲያውኑ ነበር።

ፕሬዝዳንት ኪር በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን ማቻርን ከስልጣናቸው ካነሱ በኋላ ደቡብ ሱዳን በወርሃ ታህሳስ 2013 ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ገብታለች።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ኪር፣ ማቻር መፈንቅለ መንግሥት እያሴሩ ነው ብለው የወነጀሏቸው ቢሆንም ማቻር ግን አስተባብለዋል።

በደቡብ ሱዳን የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ፖለቲካዊ አለመግባባት የፈጠረው ቢሆንም የብሔር መልክና የኃይል ክፍፍል መልክም ነበረው።

የደቡብ ሱዳን ሁለት ትልልቅ ብሔሮች፣ ዲንካና ኑዌር፣ ሁለቱ የፖለቲካ አመራሮች የተገኙባቸው ሲሆን አንዳቸው ሌላኛቸውን የብሔራቸውን ተወላጆች ማጥቃታቸውን በመጥቀስ ይወነጃጀላሉ።

የሠላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ለምን አስቸገረ?

ሁለቱ ፓርቲዎች በ2018 የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በሚል የቀረበው የሠላም ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ወይንም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ይህ ስምምነት በ2019 ግንቦት ወር ላይ የነበረ ቢሆንም ሁለቴ ለሌላ ጊዜ ተላልፎ ለየካቲት 14 (ፌብርዋሪ 22) የመጨረሻ የሚል ቀን ተቆርጦለታል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

እኤአ ከ2016 ጀምሮ ሪክ ማቻር በቋሚነት በጁባ አይቀመጡም

በአገሪቱ ያለው ግጭት ወደለየለት የሰብዓዊ ቀውስ ከቷት ቆይቷል። ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይህ ቢሆንም ፓርቲዎቹ ግን የሰላም ስምምነት ላይ በመድረስ አገሪቱን ለማረጋጋት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሁለቱ ጎምቱ ተቀናቃኞች በመካከላቸው ከፍተኛ አለመተማመን ያለ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን ከስልጣን ካሰናበቱ በኋላም አብረው ለመሥራት የሚያስችል ግንኙነት የለም።

ማቻርም ለደህንነታቸው በመስጋት በቋሚነት ጁባ ተቀምጠው አያውቁም። በ2013 ከስልጣን ከተሰናበቱ በኋላ አገር ለቅቀው የሄዱ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው የ2016 የሰላም ስምምነቱ መፍረሱን ተከትሎ ማባሪያ በሌለው ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

የሰላም ስምምነቱ የሚጠበቀውን ውጤት ያስገኛል?

እስከ አሁን ድረስ ብቻ ከ10 በላይ የሰላምና የተኩስ አቁም ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን ነገር ግን የታለመውን ሠላምና መረጋጋት ባለመስጠቱ አሁንም ምንም ማረጋገጫ የለም። ከዚህ በፊት የተደረጉ ስምምነቶች በአጠቃላይ በሙሉ መፍረሳቸውን ለተመለከተ በዚህ ስምምነትም እርግጠኛ መሆን አይችልም።

ታዛቢዎች እንደሚሉት አሁንም ደቡብ ሱዳን በተለመደው የሠላም ድርድርና የስምምነት አዙሪት ውስጥ ናት።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) አገሪቱን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ድሃ አገራት ተርታ መድቧታል።

የአገሪቱ በርካታ ክፍሎች በመንገድ ያልተሳሰሩ ሲሆን፤ በአገሪቱ በአግባቡ የተሠራው መንገድ ከ300 ኪሎ ሜትር አይበልጥም ተብሏል። ከደቡብ ሱዳን ከተሞች ውጪ ንፁህ ውሃም ሆነ መብራት ማግኘት አይቻልም።

የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት ድርጅት፤ በአገሪቱ ከሚገኙ ሕፃናት 70 በመቶ ያህሉ ከትምሀርት ቤት ውጪ መሆናቸውን ገልጿል።

ደቡብ ሱዳን ምርታማ በሆነ የሚታረስ መሬት፣ በወርቅ፣ በእንቁ እና በነዳጅ የበለፀገች አገር ብትሆንም ከአገሪቷ አጠቃላይ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ነው።