በቡናም በመልካም ተሞክሮዎችም ሰዎችን የሚያነቃቃው ወጣት

ፊልሞን ተስፋስላሴ በካፌው ውስጥ በሥራ ላይ
የምስሉ መግለጫ,

ፊልሞን እና ጓደኞቹ ካፌውን ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲከፍት ሁሉም ያላቸውን ከኪሶቻቸውን አዋጥተው ወደ ሠላሳ ሺህ ብር ገደማ አሰባስበው ነበር

ፊልሞን ተስፋስላሴ ይባላል። ቡና መቁላት እና መቅመስ ሙያው ነው። በአገረ ቱርክ ለስድስት ወራት ያህል ስልጠና ወስዶ የስራ ልምምድም አድርጓል፤ ከዚያ መልስም የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የሚሰጠውን የሦስት ወራት ስልጠና ተከታትሎ ቡናን የመቅመስ እና የመቁላትን ሙያዊ ዕውቅናን አግኝቷል።

ሙያው በተለይ ወደውጭ አገር የሚላክን ቡና በተገቢው ልኬታ መቁላትን እንዲሁም የጥራት ደረጃውን ለመለየት መቅመስን እንዲካን አስችሎታል።

ይህ ከቡና ጋር ያለው ቅርርብ ነው ለአሁን ሥራው መንገድ የጠረገው።

አሁን ከዕለታዊ ጊዜው ሰፋ ያለውን የሚወስደው በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ በሚባለው አካባቢ ከጓደኞቹ ጋር በአንድ የቀድሞ መጋዘን የከፈተውን ካፌ ማስተዳደር ነው።

ካፌው የአካባቢው ወጣቶች ቡና ከመጠጣት ባሻገር ነፃ የዋይፋይ አገልግሎት የሚያገኙበት፥ ተደርድረው ከተቀመጡ መፅሐፍት ያሻቸውን ተውሰው የሚያነቡበት እንዲሁም በወር አንዴ የሚያነቃቁ ንግግሮችን የሚያደርጉ እንግዶች ተጋብዘው የህይወት ተሞክሯቸውን የሚያጋሩበት እና የጃዝ ሙዚቃ ምሽቶች የሚስተናገዱበት ስፍራ ነው።

ቡና ለኢትዮጵያዊያን አነቃቂ መጠጥ ብቻ አይደለም ይላል ፊልሞን፤ የኑሮ ዘይቤም ነው። በተለይ ቀደም ባለው ጊዜ "የማኅበራዊ ክንውኖች ማዕከል ነበር። ሰዎች ተገናኝተው መረጃ የሚቀባበሉበት፥ ሕይወት የሚከሰትበት መናኸሪያ ነበር። በደስታ በሐዘንም ሰዎችን አንድ አድርጎ የሚያሰባስብ ስርዓት ነበር" ሲል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ያስታውሳል።

ፊልሞን ይህ ቡና ተፈልቶ፣ ሰብሰብ ብሎ ኃሳብን የመቀያየር ልማድ በከተሞች አካባቢ እየጠፋ መምጣቱ እንደሚያስቆጨው ይገልፃል፤ ከጓደኞቹ ጋር በከፈተው ካፌ እየታጣ ነው የሚለውን ማኅበራዊ ስሜት ለመኮረጅ የሚጥር ይመስላል።

የምስሉ መግለጫ,

ፊልሞን እና ጓደኞቹ ካፌ የከፈቱበት ቦታ ከሁለት ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ተዘግቶ የከረመ መጋዘን ነበር

መጋዘኑ. . .

አሁን ፊልሞን እና ጓደኞቹ ካፌ የከፈቱበት ቦታ ከሁለት ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ተዘግቶ የከረመ መጋዘን ነበር።

ዝግ በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ቆሻሻ ይጣል እና ይከመርበት፣ ሥራ የሌላቸው ወጣቶችም እርሱ "አልባሌ" ያለቸውን ተግባራት ይከውኑበት ነበር።

"ቦታው ለመጥፎ ነገር የተጋለጠ አካባቢ ነበር" ይላል።

ቦታውን በዚህ መልኩ ቀይሮ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ግን የነበረው ውጣ ውረድ ታዲያ ቀላል አልነበረም።

የመጀመሪያው ፈተና ቦታው ላይ መጋዘኑን ራሱን የመስሪያ ቦታ ለማድረግ ፈቃድ ማግኘት ነበር።

"በእኛ አዕምሮ ለሁለት ዓመታት ተዘግቶ የቆየን መጋዘን ለሚሰራ ሰው መስጠት ቀላል ውሳኔ የሚሆን ነበር የመሰለን" ይላል በወቅቱ እርሱ እና ጓደኞቹ የነበራቸውን እሳቤ ሲያስታውስ።

መጋዘኑ በአካካቢው የመንግስት አስተዳደር ባለቤትነት የተያዘ በመሆኑ፣ ከሚመለከተው አካል የመስሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሰባት ወራት ገደማ መመላለስን ጠይቆታል።

"አንደኛው እና ዋናው ችግር እርሱ ነበር፤ ሰዎች እንዲሰሩ መፍቀድ። ለዚያው ኃላፊነቱን ራሳቸው ወስደው፣ ሊመጣ የሚችለውን ኪሳራ ራሳቸው ተጋፍጠው እና በራሳቸው ወጭ እንስራ ላሉ ሰዎች።"

ፈቃዱ ከተገኘም በኋላ ሌሎች ተግዳሮቶች አፍጥጠው መጠበቃቸው አልቀረም።

ለምሳሌ መጋዘኑ ዘለግ ላለ ጊዜ ተዘግቶ እንደመቆየቱ ውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የመሳሰሉ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች አልነበሩትም።

እነርሱን ለማሟላትም የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ደጋግሞ ደጅ መጥናት አስፈልጓል።

ቦታው ቡና ይቆላበታል፤ ይፈላበታል፤ ይታሸግበታል፤ ምግብ ይሰናዳበታል። "እንደዚያ ቆሻሻ የነበረን ቦታ አሁን ለምግብ ማቀነባበሪያነት ነው የተጠቀምንበት። ሙሉ በሙሉ ነው የለወጥነው።"

በበርካታ ጀማሪ የንግድ ተቋማት ላይ የሚስተዋለው የብድር አገልግሎት እጦት ሌላኛው ማነቆ ነበር።

ፊልሞን ለወጣቶች እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ አደረጃጀት ለተዋቀሩ የንግድ እና የአገልግሎት ተቋማት ከመንግስት ይሰጣል የሚባለውን ብድር ማግኘት "ላም አለኝ በሰማይ..." ላይ ነው የሆነብን ይላል።

"የሚታይ ለውጥ አምጥተናል። ማስያዣ አለን። አርዐያ መሆን የምንችል ተቋም ነን። ይሄንን ለእነርሱ ማብራራት ራሱ ችግር ነው።"

የበጎ እሳቤ መድረክ. . .

ፊልሞን በካፌው ውስጥ መፅሐፍትን ደርድሮ ማንበብ ለሚፈለግ ሰዎች እንዲዋሱ የማድረግ ኃሳብ ከተገልጋዮች እንደመጣ ይናገራል።

መፅሐፍቱንም እንዲሁ ከደንበኞች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሰባሰበ ለቢቢሲ አስረድቷል።

"መልሶም የሚጠቀመው የአካባቢው ማኅበረሰብ ነው።"

በቀን ሁለት መቶ ገደማ ደንበኞች ቦታውን ይጎበኛሉ።

በወር አንዴ የሚከናወነው የማነቃቂያ መርኃ ግብር ግን ከራሱ የሕይወት ተሞክሮ መመዘዙን ይገልፃል።

"እኔ እንደወጣት ያለፍኩባቸው፥ የተነቃቃሁባቸው፥ የተጠቀምኩባቸው ብዙ ተመሳሳይ መርኃ ግብሮች ነበሩ።"

ሰዎች ያለፉበትን ውጣ ውረድ፣ ተሞክሯቸውን መስማት እና ምስክርነታቸውን ማዳመጥ ከምክርም በዘለለ እንደሚለውጥ በራሴም ሕይወት ላይ አይቼ አውቀዋለሁ ይላል ፊልሞን።

እናም "ሰው እንጋብዛለን፤ ልምዳቸውን፣ የስኬት ታሪካቸውን ይነግሩናል።"

መርኃ ግብሩን ማድረግ ከጀመሩ አንስቶ ከሰባት ላላነሱ ጊዜያት አከናውነዋል እርሱ አንደሚለው።

የወደፊት ጉዞ

ፊልሞን እና ጓደኞቹ ካፌውን ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ሲከፍት ሁሉም ያላቸውን ከኪሶቻቸውን አዋጥተው ወደ ሠላሳ ሺህ ብር ገደማ አሰባስበው ነበር። የነበራቸው መሣርያም ከማሽን ጎን የምትቀመጥ ትንሽ የኤስፕሬሶ መፍጫ ብቻ ነበረች።

ቡናውን ለማስቆላት ግን ማሽኑ ላላቸው ሌሎች ድርጅቶች መክፈል ነበረባቸው።

በጊዜ ሒደት ያገለገሉ ማሽኖችን ረከስ ባለ ዋጋ በመግዛት ቡናውን ራሳቸው መቁላት ጀመሩ።

አሁን በራሳቸው ቡናውን ቆልተው፥ ያፈላሉ፥ ለገበያ የሚቀርብ ዱቄትም ፈጭተው ያሽጋሉ።

የተቆላ እና የተፈጨ ቡናቸውን ለአርባ የተለያዩ ካፌዎች ያቀርባሉ- ፊልሞን ለቢቢሲ እንደገለፀው።

የባለቤትነት ድርሻ ያላቸውን እንዲሁም ተቀጥረው የሚሰሩትን ጨምሮ ለአስራ አራት ወጣቶች ቋሚ የእንጀራ በር ከፍተዋል።

በዚህ የመቆም ፍላጎቱ ግን የላቸውም።

ምርታቸውን ወደውጭ አገራት ለመላክ ፈቃዱን ወስደዋል፤ የሚቀረው አቅም ማደበር ነው።

ቡናን በመቁላት እና በመቅመስ የወሰዳቸው ትምህርቶች እና የሥራ ተሞክሮዎች "በጣም ጠቅመውናል" ባይ ነው ፊልሞን። "ከዕውቀት ተነስተን እንድንሰራ፥ የሚጎድለንን እንድናሻሽል፥ ጥራትን እንድንሽት ረድቶናል።"