በርኒ ሳንደርስ ፑቲንን 'በአሜሪካ ምርጫ ምን ጥልቅ አረጎት' አሏቸው

ቭላድሚር ፑቲን እና በርኒ ሳንድረስ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቭላድሚር ፑቲን እና በርኒ ሳንድረስ

በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሊፋለሙ ይችላሉ ተብለው ከቀረቡ ዴሞክራቶች አንዱ የሆኑት በርኒ ሳንደርስ፤ ሩስያ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ልትረዳቸው መሆኑን የሚጠቁም መረጃ መውጣቱን ተከትሎ፤ ሩስያን "ከአሜሪካ ምርጫ እጅሽን አውጪ" ሲሉ ኮንነዋል።

የ 78 ዓመቱ በርኒ እንደተናገሩት፤ ሩስያ ለምርጫ ቅስቀሳቸው ድጋፍ ለማድረግ እንደሞከረች እንደሆነ ባለፈው ወር የአሜሪካ ባለስልጣኖች አሳውቀዋቸዋል።

ሩስያ በምን መንገድ ለመርዳት እንዳሰበች ግልጽ እንዳልሆነ ተናገረው፤ ማንኛውንም አይነት ጣልቃ ገብነት በፅኑ አወግዛለሁ ብለዋል።

የሩስያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲንን "አምባገነን፣ አመፀኛ" ካሉ በኋላ "በኢንተርኔት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት አገራችንን ለመከፋፈል እየሞከረ ነው" ሲሉ አብጠልጥለዋቸዋል።

"ሩስያውያኑ እኛን በመከፋፈል ዴሞክራሲያችንን ለማንኳሰስ እንደሚፈልጉ መታወቅ አለበት። አሁን ስልጣን ላይ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ስላልሆንኩ የሩስያን በምርጫችን ጣልቃ መግባት አወግዛለሁ" ሲሉም ተደምጠዋል።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር በተያያዘ ወቀሳ እየዘነበባቸው ነው

ትራምፕ ፑቲን አሜሪካን እንዲጎበኙ ጋበዟቸው

ሩስያ ትራምፕን ዳግመኛ ለማስመረጥ እየሞከረች መሆኑ ተጠቆመ

በርኒ ሳንደርስ የዴሞክራቶች እጩ ለመሆን ሰፊ እድል አላቸው። ፌስቡክ እንዳለው ከሆነ፤ ሩስያ ለበርኒ ቅስቀሳ ድጋፍ ስለማድረጓ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው፤ ሩስያ በርኒን ለመርዳት ጥረት እያደረገች መሆኑ ለትራምፕና ሌሎችም የአገሪቱ ባስልጣኖች ተገልጿል።

በሌላ በኩል ሩስያ ትራምፕን በድጋሚ ለማስመረጥ በአሜሪካ ፖለቲካ እጇን ለማስገባት እየሞከረች መሆኑን የአገሪቱ የደህንነት ተቋም ኃላፊዎች መናገራቸው ይታወሳል።

በህዳር ወር በሚካሄደውን ምርጫ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ለማድረግ ሩስያ እየጣረች መሆኑ በምክር ቤቱ የደህንነት ኮሚቴ መገለጹንም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን ዘገበዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው "ዴሞክራቶች የነዙት ተራ አሉባልታ ነው" ብለዋል።