ሰሜን ኮሪያ ኮሮናቫይረስ እንዳይዛመት በመስጋት የውጭ ዜጎችን ማቆያ ጣብያ እያስገባች ነው

ሰሜን ኮሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰሜን ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመስጋት 380 ያክል የውጭ ዜጎችን በማቆያ ጣብያ ውስጥ ማስገባቷ ተነገረ።

አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ዲፕሎማቶች ሲሆኑ በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በሚገኝ ጣብያ ውስጥ ነው እንዲቆዩ የተደረገው ሲል የኮሪያ ማዕከላዊ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ጠቅሶ ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘግቧል።

200 ገደማ የውጭ ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ከሚኖሩበት ግቢ ንቅንቅ እንዳይሉ ተደርገው እንደነበር፤ አሁን ግን እንደተለቀቁ ተነግሯል። ቢሆንም በርካቶች ወደ ማቆያ ጣብያዎች እየተጋዙ ነው።

በሰሜን ኮሪያ፤ እስካሁን አንድም የተዘገበ የኮቪድ-19 ተጠቂ የለም። የውጭ አገር ዜጎቹ በለይቶ ማቆያው ጣብያው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ የተነገረ ነገር የለም።

ጎረቤት አገር ደቡብ ኮሪያ 763 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 7 ሰዎች ሞተዋል። 11 ወታደሮች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ተከትሎ 7700 የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች በማቆያ ጣብያ እንዲቆዩ መደረጉም ተሰምቷል።

ቻይና የተከሰተው ኮሮናቫይረስ ወደ 29 አገራት ተዛምቷል። አውሮጳ ውስጥ በርካታ የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ያላት አገር ጣልያን ናት። 152 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ለሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ መደረጉም አይዘነጋም።

ኢራን ውስጥ ደግሞ 43 ሰዎች ተይዘው 8 ሰዎች ሞተዋል።

ቻይና ውስጥ በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ከ2500 በልጧል። 77150 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ከቻይና ጋር ወደብ የምትጋራው ሰሜን ኮሪያ በቫይረሱ የተጠቃ ዜጋ ባይኖርባትም ስጋት ግን ሳይገባት የቀረ አይመስልም። ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚያመራ ማንኛውም ዜጋ ለ30 ቀናት በለይቶ ማቆያ ይቆያል።

ነገር ግን ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚያመሩ የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር እጅግ ውስን ነው። ስማቸውን እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለሙያ በሰሜን ኮሪያ የሚገኙት የምዕራባውያን አገራት ዜጎች ቁጥር ከ 200 አይዘልም ብለዋል።

አልፎም የሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናት ለወትሮው በርካታ የውጭ አገር ዜጎች የሚሳተፈበት የፒዮንግያንግ ማራቶን ዘንድሮ እንዳይከናወን አዘዋል።

ከቻይና ጋር ደንበር በምትጋራው የሰሜን ፒዮንጋን ግዛት የሚኖሩ 3000 ሰዎች የቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው እንደሆነም ተዘግቧል።