ዶናልድ ትራምፕን ሕንድ ድረስ ያስኬዳቸው ምንድነው?

ሞዲ ትራምፕና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ትራምፕና ባለቤታቸው ነጠላ ክር እየደወሩ ይታያሉ፤ ማህተማ ጋንዲ የሚያጣፉትን ነጠላ ለማሰብ በሚል

ለትራምፕ 36 ሰዓታት ከአሜሪካ ርቆ መሄድ ቀልድ አይደለም። ለሕንድ የሰጡትን ቦታ የሚያሳይ ነው። ሞዲና ትራምፕ ፍቅራቸው አይሏል።

ይህን የሚያመላክቱ ብዙ ኩነቶችን መጥቀስ ይቻላል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ትራምፕ ሞዲን በስስት ሲመለከቱ ይታያሉ

ትራምፕ ሕንድን ሊጎበኙ ነው ከተባለ ጊዜ አንስቶ ሕንድ ጭርንቁስ ሰፈሮቿን በሸክላ ጡብ ስታሽጋቸው ነበር። "የአገሬው ጋዜጦች እነዚህን የድህነት ግድግዳዎች "ትራምፕ ዎል ኢን ኢንዲያ" እያሉ ሲሳለቁባቸው ነበር።

እርግጥ ነው ትራምፕ ድሀና ድህነትን ማየት የሚፈልጉ ዓይነት መሪ አይደሉም። የሚማርካቸው ድህነትን አሸንፎ መውጣት ነው። ሁሌም የሚሰብኩት ታላቅ መሆን። ሞዲና ትራምፕ አንድ የሚያመሳስላቸውም ይኸው ነው፤ ሁለቱም ለሕዝቦቻቸው "ትልቅ ነበርን፤ ትልቅን እንሆናለን" ይላሉ፤ መልሰው መላልሰው።

ትራምፕ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ሞዲ ጠበቅ አድርገው ነው ያቀፏቸው። በአህማዳባድ ከተማ የማህታማ ጋንዲ ቤት እስኪደርሱ ድረስ የሕንድ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ለትራምፕ አንድ ጊዜ ሲያጨበጭብ፣ ሌላ ጊዜ ሲያውለበልብ ነበር።

ከዚያ በዓለም ትልቁን የክሪኬት ስታዲየም መርቀዋል። የሕዝብ እጥረት የሌለባት ሕንድ ስታዲየሙን ሞልታ ትራምፕን በደማቅ ተቀብላለች።

ከወራት በፊት ሞዲ አሜሪካንን ሲጎበኙ 125ሺ ሰው ትራምፕ ስማቸውን እየጠራ ዘምሮላቸዋል።

በተደጋጋሚ ሲተቃቀፉ ታይተዋል። በተደጋጋሚም ይደናነቃሉ።

ትራምፕ ስለሞዲ ሲናገሩ "ሁሉም ሰው ሞዲን ይወደዋል፤ ነገር ግን ቀላል ሰው እንዳይመስላችሁ፤ ጠንካራ መሪ ነው፤ የጉጅራት ኩራት ብቻ አይደለህም ሞዲ፤ አንተ አንድ ነገር ለማሳካት ምንም እንደማይሳን ማሳያ ነህ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ትራምፕና ባለቤታቸው ዛሬ ታጅ መሀልን ጎብኝተዋል

ትራምፕ አንድ ቦታ ላይ እንዲያውም "ፈጣሪ አሜሪካንን ይባርክ፤ ሕንድንም ይባርክ" ሲሉ ተሰምተዋል። "እግዚአብሔር ሌላ አገርንም ይባርክ" የሚል ንግግር ለያውም ትራምፕን ከመሰለ ፅንፈኛ ብሔርተኛ መሪ እምብዛምም የተለመደ አይደለም።

ዛሬ ከሰዓት ደግሞ ትራምፕ የክብርት ባለቤታቸውን ቀዳማዊት እመቤት ሜላንያ ትራምፕን እጅ በፍቅር ይዘው "የፍቅር ተምሳሌት" የሚባለውን ታጅ ማሃልን ጎብኝተዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ሞቴራ ስታዲየም 125ሺ ተመልካች የሚይዝ የዓለም ትልቁ የክሪኬት ስታዲም ነው፤ትራምፕ መርቀውታል

የሁለቱን አገራት ፖለቲካዊ ታሪክ በቅርብ የሚከታተሉ አዋቂዎች የሚከተሉትን ምክንያቶች ሞዲና ትራምፕ ፍቅራቸው እንዲጎመራ አድርገዋል ይላሉ።

1ኛ፦ንግድ

አሜሪካ የሕንድ ጥብቅ የንግድ አጋር ናት። የንግድ ልውውጣቸው ባለፈው ዓመት 142 ቢሊዮን ደርሶ ነበር ። ሆኖም የታሪፍ ጉዳያቸውን በሰላም አልፈቱትም። ትራምፕ "ሕንድም የቻይናን ያህል ባይሆንም አላግባብ እየተጠቀመችብን ነው" ብለው ያምናሉ። ትራምፕ ይህንን መለወጥ ይፈልጋሉ።

2ኛ፦የትወልደ ሕንዳዊያንን ልብ ማሸነፍ

ትራምፕ ለ2ኛ ዙር አራት ዓመት አሜሪካንን ለመምራት ከአመት ባነሰ ጊዜ ምርጫ ይጠብቃቸዋል። ሕንዳዊያን በአሜሪካን አገር ፈሰዋል። ቁጥራቸው 4̋ ሚሊዮን ያልፋል። የነዚህን ልብ ማሸነፍ ይፈልጋሉ ትራምፕ። ትውልደ ሕንዳዊያን በአመዛኙ ድምጽ የሚሰጡት ለዲሞክራቶች ነው። 16 ከመቶ ትውልደ ሕንዳዊያን ብቻ ናቸው በባለፈው ምርጫ ለትራምፕ ድምጽ የሰጡት።

3ኛ፦ ትራምፕ ለተቀረው ዓለም ግድ የላቸውም የሚለውን አስተሳሰብ መለወጥ

ትራምፕ ተቺዎቻቸው አሜሪካንን በዓለም አቀፍ የነበራትን ተሰሚነትና ጤናማ ግንኙነት እንዲሳሳ፣ እንዲኮስስ አድርገዋል ይሏቸዋል። ትራምፕ ይህንን መቀየር ይፈልጋሉ። የምርጫ ሰሞንም አይደል? የአሜሪካ ድምጽ ሰጪዎች ትራምፕ በሌላ አገር የሚደረግላቸው አቀባበልና ፍቅር ሊገዛቸው ይችላል። ይህ የሞዲና የሕዝባቸው የሞቀ አቀባበል አገር ቤት ሲመለሱ ለምርጫ ቅስቀሳ ይጠቀሙበታል።

4ኛ፦ ቻይናን ማስደንገጥ

እንደ ትራምፕ ቻይና ላይ የጨከነ መሪ የለም። የሁለቱ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሃገራት ወደ ምጣኔ ሀብት ጦርነት እንዳይሸጋገር አለም ተጨንቆ ነበር። ምክንያቱም የቻይናና የአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ጦርነት ዳፋው ለድሀ አገራት ስለሚተርፍ ነው። በመጨረሻ የተፈራው ሳይሆን ቀርቶ የመጀመርያ ዙር ስምምነት ከቻይና ጋር ፈርመዋል ትራምፕ።

የቻይና በዓለም አገራት ያላት ተሰሚነት መጨመር ግን ትራምፕን እረፍት ነስቷቸዋል። ዘቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ የሚባለውና አገራትን በመንገድና መሠረት ልማት ከቻይና ጋር ለማስተሳሰር የተጀመረው ፕሮጀክት የሆነ ቦታ እንዲቆም ይፈልጋሉ ትራምፕ። ይህ ህንድም የምትፈልገው ነገር ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ሞዲ ትራምፕን በተደጋጋሚ እየተወረወሩ ሲያቅፏቸው ታይተዋል

ቻይናና አሜሪካ በምጣኔ ሀብት ቢቋሰሉ ሕንድ ታተርፋለች ማለት አይደለም። ሆኖም የሁለቱ እጅግ መቀራረብም ለሕንድ መልካም ዜና አይደለም። የሕንድ አስፈላጊነት እየሳሳ ይመጣል፤ ስለዚህ ሕንድ ጤናማ ግንኙነትን ከአሜሪካ ጋር ስትመሰርት የቻይናንም የአሜረካንንም ትሩፋት ማጣጣም ትችላለች።

ትራምፕ የቻይና ነገር ከቁጥጥር ውጭ ቢወጣ በእስያ በርካታ ሕዝብ ያለው፣ ኢኮኖሚው ለአሜሪካ የሚመጥን፣ ሰፊ ገበያ ያለው አስተማማኝ ማስፈራሪያ ይፈልጋሉ፤ ያቺ አገር ደግሞ ሕንድ ናት።

5ኛ፦የጦር መሣሪያ ግዥ

ለአሜሪካ የጦር መሣሪያ ደንበኛዋ ሳዑዲ ናት። ሕንድም የዋዛ አይደለችም። ትራምፕ ጉብኝታቸው በቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ስምምነት እንደሚቋጩ እየተነገረ ነው። ይህ በአገር ቤት ነጥብ ያስቆጥርላቸዋል። በምርጫ ቅስቀሳም የገንዘብ መጠኑን እየጠቀሱ ወደ አሜሪካ ካዝና ያስገቡትን አዱኛ ይዘረዝራሉ።

ገና ትራምፕ ወደ ሕንድ ከማቅናታቸው በፊት እንኳ የአየር መቃወሚያ ግዥ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት በሂደት ላይ ነበር። ሕንድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጦር መሣሪያ የምትሸምትው ከሩሲያና ከፈረንሳይ ነበር። ሩሲያ ከዚህ ስሌት እንድትወጣ ትራምፕ ይሻሉ።

በአጠቃላይ ትራምፕና ሞዲ የሚሰምር ግንኙነት አንድ ያሉ ይመስላል። ትራምፕ ወደ ሕንድ ከማቅናታቸው በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ሕንድ እኛን የምትንከባከብ አገር አይደለችም፤ ሆኖም ሞዲን ወድጄዋለሁ" ብለው ነበር።

የዲፕሎማቲክ ተንታኞች እንዲህ ብለው ይደመድማሉ፤ "የሁለቱ በግል መቀራረብ ጠጣር ለሚባሉ የፖሊሲ ጉዳዮች ፈውስ ነው፤ ድሮም ትራምፕ በባህሪያቸው ለሚወዱት ሟች ናቸው"