ዓለም ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዘጋጀት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

ደቡብ ኮሪያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዓለም ጤና ድርጀት ኮሮናቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋ ስለሚችል አገራት በሚገባ እንዲዘጋቹ አሳስቧል። ምንም እንኳ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሮናቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ ሆኗል ብሎ ለማወጅ ገና ቢሆንም አገራት ግን በቂ ዝግጅት የማድረግ ሂደት ውስጥ መሆን ይገባቸዋል ብሏል ድርጅቱ።

የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳው ኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ በደቡብ ኮሪያ እና በጣልያን የተቀሰቀሰ ሲሆን በኢራንም ከፍተኛ ስጋት አለ።

ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ቻይና 77 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ2600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሞተዋል። 1200 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በ30 አገራት በቫይረሱ መያዛቸው ሲመዘገብ 20 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

በጣልያን ቀደም ሲል ሶስት ሰዎች በቫይረሱ ሞተው የነበረ ሲሆን ትናንት ደግሞ ሌሎች አራት ሰዎች መሞታቸውን መንግስት አስታውቋል።

ቫይረሱ ከፈጠረው ስጋት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአክሲዮን ሽያጭ አሽቆልቁሏል።

ትናንት ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ኩዌት፣ ኦማን እና ባህሬን ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ማግኘታቸውን ሪፖርት አድርገዋል።

በባህሬን ቫይረሱ የተያዘው የተማሪዎች ማመላለሻ አውቶቡስ ሹፌር ስለሆነ በዚህ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደነበሩ ታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትናንት በቅርብ ቀናት በኢራን፣ ጣልያን እና ደቡብ ኮሪያ ከቫይረሱ ጋር የታየው ነገር እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

"መተላለፍ ያለበት ዋናው መልዕክት ለአገራት ተስፋ የሚሰጥ እና ይሄ ቫይረስ በቁጥጥር ስር መዋል የሚችል እንደሆነ የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል" ብለዋል።

ቫይረሱ ወረርሽኝ የመሆን ድል አለው? ለሚለው የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም መልስ "አዎ በርግጠኝነት" የሚል ነው። አሁን ግን እዚያ ደረጃ ላይ አልተደረሰም ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ የጤና ጉዳዮች መርሃግብር ሃላፊ ማይክ ራያን ግን "ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርጉትን ዝግጅት ሁሉ አድርጉ" በማለት ለአገራት ጠንካራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።