የኮቢ ብራያንት ባለቤት የተከሰከሰው ሄሊኮፕተር ባለቤትን ከሰሰች

ብራያንት እና ልጁ ጊያና Image copyright Getty Images

ባለፈው ወር በሄሊኮፕተር አደጋ ባለቤቷ እውቁ ኮቢ ብራያንትን እና የ13 ዓመት ሴት ልጇን ያጣችው ቫኔሳ ብራያንት፣ በሄሊኮፕተሩ ባለቤት ላይ የመሰረተችው ክስ ጭብጥ በመጥፎ የአየር ሁኔታ ለመብረር መወሰኑ የአብራሪውን ግድየለሽነት ያሳያል የሚል ነው።

የሄሊኮፕተሩ ባለቤት አይላንድ ኤክስፕረስ ሄሊኮፕተሮችና አብራሪዎች የተሰኘ ድርጅት ሲሆን፣ ፓይለቱ አራ ጆርጅ ዞባያን ማንኛውም ጠንቃቃ አብራሪ ሊያደርግ የሚገባውን ጥንቃቄ መውሰድ ነበረበት ይላል የቀረበው ክስ።

ክሱ እንደሚለው በሄሊኮፕተሩ አደጋ ከኮቢ ብራያንት እና ልጁ ጋር የሞተው የሄሊኮፕተሩ አብራሪ ዞባያን ለበረራ ሲዘጋጅ የአየር ሁኔታ ትንታኔን ከግምት አላስገባም።

አብራሪው ሁኔታዎች ከባድ ሆነው እያለም በራራውን ለማቋረጥ አልወሰነም፤ ለበረራው የይለፍ ፍቃድ የሰጠው አይላንድ ኤክስፕረስም ሄሊኮፕተሩ አስቻጋሪ በሆነ የአየር ሁኔታ እንደሚበር እያወቀ ፍቃድ ሰጥቷል ሲል ክሱ ያትታል።

ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ለጊዜው የተቀመጠ የገንዘብ መጠን ባይኖርም ቫኔሳ ብራያንት ከኩባንያው ካሳና ኩባንያው በወንጀል እንዲቀጣም ትፈልጋለች።

ታዋቂው አሜሪካዊ ስፖርተኛ ከነልጁ በሄሊኮፕተር አደጋ ሞተ

2019 የአውሮፕላን አደጋ ተጎጂዎች ቁጥር የቀነሰበት ነው ተባለ

ከ33 ዓመት በፊት የተዘረፈው ዘውድ ለጨለቆት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንደሚመለስ ተገለጸ

ኮቢ እና ልጁን ይዞ የነበረው ሄሊኮፕተር ካላባሳስ ከተሰኘች ከተማ ከከፍታማ ቦታ ቁልቁል ወርዶ መከስከሱ ቀደም ሲል ተገልጿል።

ሄሊኮፕተሩ በተነሳበት ወቅት የአየሩ ሁኔታ ጭጋጋማ ነበር።

ምንም እንኳ የአየር ሁኔታው ከባድ የነበረ ቢሆንም ፓይለቱ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ልዩ ፍቃድ በመጠየቅ እና ፍቃዱን በማግኘት መብረሩም ተገልጿል።

አይላንድ ሄሊኮፕተርስ በአሁኑ ወቅት በረራ አቋርጧል።

ትናንት በርካታ ሥመ ጥር ሰዎች በተገኙበት ኮቢ እና ልጁ ጊያና ተዘክረዋል። መርሃግብሩን ቢዮንሴ ብያንት ይወደው ነበር ባለችው ዜማዋ ጀምራለች።

እንደ ማይክል ጆርዳን፣ ማጅክ ጆንሰን እና የብራያንት የቀድሞ ክለብ ጓደኛ የሆነው ሻኪል ኦኒል ያሉ የቅርጫት ኳስ ኮከቦች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል።