በ30 የኢትዮጵያ ወረዳዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱ ተገለፀ

የሚከተብ ህፃን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ30 የኢትዮጵያ ወረዳዎች የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱን ገለፀ። እስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት መሞታቸው ታውቋል።

ሦስቱ የሞቱት ሰዎች ወረርሽኙ በተከሰተባቸው 30 ወረዳዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ መሆናቸውን የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት እና ምላሽ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ 30ዎቹ ወረዳዎች በስድስት ክልሎች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። እነዚህም ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ አፋር፣ ሶማሊ እና ትግራይ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ኃላፊው ለቢቢሲ እንደገለፁት፤ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው ወረዳዎች የሚገኙት በገጠራማ የክልሎቹ አካባቢ ነው።

በወረርሽኙ የተጎዱት አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የሚገኙት ደግሞ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።

አቶ መስፍን ጨምረው እንዳሉት፤ ወረርሽኙ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የክትባት ስርጭቱ ደካማ የሆነባቸው ናቸው።

እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ በዚህ ሳምንት ብቻ 228 በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኩፍኝ ወረርሽኝ የተከሰተው ባለፈው ሕዳር ወር ላይ ነው።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በኩፍኝ ምክንያት የሰዎች ሕይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።

በወቅቱ በርካቶች በወረርሽኙ መያዛቸውንና በአንዳንድ ቦታዎች መቀስቀሱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር በየነ ሞገስ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።

እርሳቸው እንደሚሉት በሶማሌ ክልል ላይ በዋናነት ሸበሌ፣ ሊበንና ጃረር የሚባሉ ዞኖች ላይ ወረርሽኙ መከሰቱን ገልፀው በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ባሌ ላይ መዛመቱን ገልፀው ነበር።

በዓለም ዙሪያ በኩፍኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በ2018 ብቻ ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተደረገ ጥናት አመልክቶ ነበር።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸውም ተነግሯል።

የጤና ባለሙያዎች ስለዚህ ክስተት ሲገልጹ፤ በቀላሉ በክትባት መከላከል የሚቻል በሽታ የሰዎችን ሕይወት መቅጠፍ መጀመሩ በጣም አስደንጋጭና አሳሳቢ ነው ብለውታል።