ሆስኒ ሙባረክ፡ የአዲስ አበባው የግድያ ሙከራ ሲታወስ

ሆስኒ ሙባረክና የአዲስ አበባው የግድያ ሙከራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሙባረክ የካቲት 17/2012 ዓ.ም አሸለቡ። በሰላም፤ ያውም በሆስፒታል ውስጥ፤ ያውም በተመቻቸ አልጋቸው ላይ ሆነው።

እኚህ ሰው ግን ከሞት ጋር ሲተናነቁ የአሁኑ የመጨረሻቸው ይሁን እንጂ የመጀመሪያቸው አልነበረም። በትንሹ 6 ጊዜ ሞት እየመጣ 'ዘይሯቸው' ይመለሳል።

ሙባረክ በሳንጃ፣ በቢላ፣ በጥይትና በቦምብ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ከሞት መንጋጋ ያመለጡ ተአምረኛ ሰው ናቸው።

ጥቂቶቹን ዛሬ ባናስታውስ ታሪክ ይታዘበናል።

ጥቅምት 6፣1981። የዛሬ 41 ዓመት አካባቢ።

አንዋር ሳዳት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መናኺም ቤገን ጋር የካምፕ ዴቪድ ስምምነት ፈረሙ።

ኖርዌይ ኖቤል ሸለመቻቸው፤ አረቡ ዓለም ግን ዓይንህን ላፈር አላቸው፤ "ከሀዲው ሳዳት" ተባሉ። ሞት ለሳዳት ተዘመረ። ያኔ የሳዳት ምክትል ሆስኒ ሙባረክ ነበሩ።

በካይሮ አብዮት አደባባይ "ኦፕሬሽን ባድር" እየተዘከረ ነበር። ይህ ኦፕሬሽን ግብጽ እስራኤልን ድል ያደረገችበት ቀን ነው። ግብጾች የረመዳን ጦርነት ይሉታል። ታሪክ የዮም ኪፑር ጦርነት ይለዋል።

ዮም ኪፑር በአይሁድ ዕምነት የቤዛና የንስሃ ቅዱስ ዕለት ነው። ግብጾች በዚህ ቅዱስ ቀን ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝረው ስዊዝ ካናልን ተሻግረው የሲናይ በረሃ አንድ ግዛትን ከእስራኤል ነጻ ያወጡበት ቀን ነው።

ይህ ቀን በየዓመቱ ይዘከራል። ያን ዕለትም በካይሮ አብዮት አደባባይ ይኸው እየሆነ ነበር። ሙባረክና ሳዳት ተደላድለው ሰልፈኛውን ወታደር እያጨበጨቡ ይሸኛሉ።

አንድ ወታደር በኮፍያው የእጅ ቦምብ ቀርቅሮ... ከኦራል መኪና ላይ በድንገት ወርዶ አንዋር ሳዳትን ተጠጋቸው፤ እርሳቸው ደግሞ ለመደበኛ ወታደራዊ ሰላምታ መስሏቸው ፈገግ ይሉለታል። የጥይት መአት አርከፈከፈባቸው። ሳዳት ሞቱ። ሙባረክ ቆሰሉ። ሆስኒ ሙባረክ የመጀመሪያውን የሞት ቀጠሮ ለጥቂት አመለጡት።

መስከረም 7፣ 1999፤

ሙባረክ በኢንዱስትሪ የወደብ ከተማ ፖርት ሳይድ ጉብኝት ላይ ነበሩ። ሕዝቡ 'ሙባረክዬ' እያለ ይስማቸዋል። እርሳቸውም ከመኪናቸው በመስኮት ወጥተው አጸፋውን ይመልሳሉ።

አንድ ቢላ በኪሱ የሸጎጠ የ40 ዓመት ጎልማሳ ሊከትፋቸው ሰነዘረ፤ የአየር ኃይል አብራሪ የነበሩት ሙባረክ ያን ለታ ከቢላም ከሞትም አመለጡ፤ እጃቸው ላይ ብቻ ቆሰሉ። ከብርሃን የፈጠኑት ጠባቂዎቻቸው ሰውየውን በዚያው ቅጽበት ከሕይወት ወደ ሞት ሸኙት።

ሙባረክ በቦሌ ጎዳና

ሆስኒ ሙባረክ ለሦስተኛ ጊዜ የሞት ቀጠሮ የነበራቸው በአዲስ አበባ ነበር። ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ፤ አንድ ሰማያዊ ቫን መኪና መንገዱን ዘግቶ ጥይት ማርከፍከፍ ጀመረ። ዕድሜ ለኢትዮጵያ ወታደሮች ሙባረክ ከሞት ተረፉ። እርሳቸው ግን የእኔ ደህንነቶች ናቸው ያተረፉኝ ብለዋል።

ያኔ ካይሮ ላይ ተመልሰው አዲስ አበባ ላይ ስላጋጠቸው ነገር ለጋዜጠኞች እንዲህ ብለው ነበር።

"ሊገድሉኝ የሞከሩት ሰዎች በትክክል የምን ዜጋ እንደሆኑ ልነግራችሁ አልችልም። ነገር ግን ኢትዮጵያዊ አይመስሉም፤ ጥቁርም አይደሉም። 5 ወይም 6 ቢሆኑ ነው። የተወሰኑት ጣራ ላይ ነበሩ። ገና ከቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ እንደወጣሁ ነው።

"አንድ ሰማያዊ መኪና መንገዱን ዘጋው፤ አንዱ ወርዶ መተኮስ ጀመረ። ሌሎች ከፎቅ ይተኩሱ ነበር። መኪናዬ ግን ጥይት አይበሳውም ነበር። ምንም አልደነገጥኩም። ሾፌሬ ግብጻዊ ነበር። መኪናውም የኛው ነበር። ቀኝ ወደ ኋላ ዞረህ ተመለስ አልኩት። ሦስቱን የገደሏቸው የኛ ደህንነቶች ናቸው።"

የሙባረክ አጭር የሕይወት ታሪክ

ሙባረክ የተወለዱት በሰሜን ግብጽ ካፍር አል መስለሃ ውስጥ ነው። ያን ጊዜ አንዋር ሳዳትን ሆኑ ገማል አብዱልናስር አልመጡም። በንጉሥ አህመድ ፉአድ ፓሻ ዘመን ነው የተወለዱት። ይህ ማለት ሙባረክ ተወልደው እስኪሞቱ ባሉ 91 ዓመታት ውስጥ 4 ፕሬዝዳንቶች ሲፈራረቁ አይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሙባረክ ከ'ተራ' ቤተሰብ ይምጡ እንጂ ተራ ሰው አልነበሩም። ከዝነኛው የግብጽ ወታደራዊ አካዳሚ ተመርቀዋል። አየር ኃይል ገብተው፣ ትንንሽ የጦር አውሮፕላኖችን ለሁለት ዓመት አብርረው፤ ከዚያ የአብራሪዎች አስተማሪ ሆኑ። ሥራው ግን ሰለቻቸው።

በዚህ መሀል ታላቁ ጄኔራል ጋማል አብዱልናስር ከሥልጣናቸው ሲፈነገሉ በአይነ ቁራኛ ተመለከቱ። ያን ቀን ሥልጣን ውልብ ሳትልባቸው አልቀረም።

እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ በ1959 ሙባረክ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት አቀኑ። ያኔ ሶቭየት ኅብረት ለግብጽ ሁነኛ ረዳት ነበረች። እዚያ ሄደው ቦምብ ጣይ አውሮፕላን አብራሪነት ተማሩ።

ከሶቪየት ኅብረት ሲመለሱ ሩሲያኛን አቀላጥፈው ነው። ወዲያው የአየር ኃይል አካዳሚው አለቃ ሆኑ፤ ወዲያውኑ የአየር ኃይል ዋና አዛዥነቱን ያዙ። ወዲያው መከላከያ ሚኒስትር ሆኑ። በሥልጣን ላይ ሥልጣን ደራረቡ። እርሳቸው ግን አሁንም ይበርደኛል ይሉ ነበር።

ይህ ሁሉ ሥልጣን ታዲያ እንዲሁ አልመጣም። ከእስራኤል ጋር በነበረው የ6ቱ ቀን ጦርነት በአየር ኃይል አዛዥነታቸው ብሔራዊ ጀግና ተደርገው በመታየታቸው ነው ሥልጣን እግር በግር እያሳደደ የሚከተላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህን የሙባረክን ዝና ያስተዋሉት ሳዳት በመጨረሻም ምክትላቸው አደረጓቸው። ሳዳት ሲገደሉ ሙባረክ አጠገባቸው ነበሩ። እርሳቸውን አስቀብረው፤ ቁስላቸውን አስጠግገው ወደ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገቡ።

ከዚህ በኋላ ከሞቀው ቤተ መንግሥት ለመውጣት 3 ዐሥርታት አስፈልጓቸዋል።

ከዚህ በኋላ ሙባረክ ከሀብታሟ ሳኡዲ አረቢያ ጋር ታረቁ። በሳዳት ምክንያት ከአረብ ሊግ የተባረረችው ግብጽም ወደ ህብረቱ ተመለሰች። እንዲያውም የአረብ ሊግ መቀመጫ ወደ ግብጽ ተመለሰ።

ሙባረክ የተማሩት በሩሲያ ውስጥ ነው። በሩሲያኛ ቋንቋ ይቀኛሉ። ነገር ግን ከሶቭየት ኅብረት ይልቅ ምዕራቡ ጋር የሙጥኝ አሉ።

እስራኤል ጋር አልቃረንም፤ ስምምነቱንም አላፈርስም በማለታቸው አሜሪካ ሙባረክን ወደደች። ቢሊዮን ዶላሮችን ማፍሰስ ጀመረች። ሙባረክ የጀመሩት የአሜሪካና የግብጽ ወታደራዊ ፍቅር ዛሬም ደረስ ቀጥሏል።

ሙባረክ በተለይም በመጨረሻው የአንቀጥቅጠህ ግዛ ዘመናቸው ለይቶላቸው ነበር። እርሳቸው ላይ ብዕሩን ያነሳ የካይሮ ደራሲ ይቆነጠጣል፤ በሙባረክ ቤተሰብ የተሳለቀ ኮሜዲያን ይኮረኮማል፤ ሙባረክ ታፍረውና ተከብረው ነበር የኖሩት፤ በውድም በግድም።

ከዕለታት ባንዱ ቀን የካይሮ "አብዯት አደባባይ" (ታህሪር) ተጥለቀለቀች። የአረቡ ጸደይ ከተፍ አለ።

ተንቀጥቅጦ የተገዛላቸው የንስር ሕዝብ አንቀጠቀጣቸው።

ታንክ ቢልኩ፤ ጥይት ቢያርከፈክፉ ወይ ፍንክች፤

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2011 ላይ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል ሥልጣኔን ለቅቂያለሁ አሉ። ግብጾች ዘመናዊው ፈርኦን ሥልጣን ለቀቀ ብለው በደስታ እንባ ተራጩ። የፈርኦን መሸኘት ግን ሌላ ፈርኦንን እንዳይመጣ አላደረገም።

ዛሬ ግብጻዊያን ለሙባረክ ያለቅሳሉ? ወይስ ማረን ሙባረክ ይላሉ?

ሙባረክን የሸኘው የታታህሪር አደባባይ ሬሳቸውን ሲሸኝ ምን ይል ይሆን?