ኮሮና ቫይረስ ከየት መጣ?

ፓንጎሊን Image copyright Getty Images

በቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተቀሰቀሰውና ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በመዛመት ላይ ያለው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) እንዴት ከእንስሳት ወደ ሰዎች እንደተላለፈ ለማወቅ ተመራማሪዎች ከባድ ጥናት ላይ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ያለው መላምት በቻይና ጫካ ውስጥ ከተገኘ የሌሊት ወፍ እንጥብጣቢ ፈሳሽ በራሪ ነፍሳትን ወደሚመገቡ እንስሳት ተላልፎ፣ በመጨረሻ ወደ ዱር እንስሳት ተዛምቷል የሚል ነው።

ከዚያም በቫይረሱ የተያዘ እንስሳ ሰው እጅ ወደቀ፤ ቫይረሱ ከዚህ ሰው የዱር እንስሳት መሸጫ ገበያ ውስጥ ወደሚሰሩ ሰዎች ተላልፎ በመጨረሻ የዛሬው ዓለም አቀፍ የኮሮና ስርጭት ላይ ተደረሰ።

በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች በዚህ መላምት ላይ እርግጠኛ ለመሆነ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።

በለንደኑ መካነ አራዊት ማህበረሰብ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሪው ከኒግሃም እንደሚሉት ኮሮናቫይረስ ከየት መጣ የሚለውን ነገር ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት የወንጀል ምርመራ ያህል ውስብስብ ነው ይላሉ።

በርካታ የዱር እንስሳት በተለይም የበርካታ ዓይነት ኮሮናቫይረስ ተሸካሚ የሆነችው የሌሊት ወፍ የዚህኛው ኮሮናቫይረስ አስተላላፊ እንደሆነች ይገምታሉ።

በየትኛውም አህጉር የሚገኙትና በቡድን ረዥም ርቀት የሚበሩት አጥቢ ነፍሳት ራሳቸው የመታመም እድላቸው እጅግ አነስተኛ ሲሆን ቫይረሶችን በስፋት የማስተላለፍ እድላቸው ግን ሰፊ ነው።

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጇ ፕሮፌሰር ኬት ጆንስ እንደሚሉት የሌሊት ወፎች ዘረመላቸው ቢጎዳ መልሰው መጠገን ስለሚችሉ ምንም እንኳ የብዙ ዓይነት ቫይረስ ጫና ቢኖርባቸውም ሳይታመሙ ይቋቋሙታል። እናም ይህ የሌሊት ወፎች ባህሪ ለቫይረሶች መራባትና መሰራጨት ምቹ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።

Image copyright Getty Images

የሌሊት ወፎች ቫይረሶችን ወደ ሰዎች የማስተላለፍ እድላቸውም ከፍተኛ እንደሆነ የኖትንግሃም ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጀናታን ባል ይናገራሉ።

ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በዉሃኑ የእንስሳት ገበያ ኮሮና ቫይረስን በመርጨት የተጠረጠረው እንስሳ ፓንጎሊን ነው። ጉንዳን በሊታው ፓንጎሊን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በህገወጥ መንገድ የሚሸጥ እንስሳ ሲሆን በመጥፋት አደጋ ላይ ያለ እንስሳም ነው።

ይህ እንስሳ እስያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ለመድሃኒትነት ይፈለጋል። በሌላ በኩል የፓንጎሊን ስጋ ለበርካቶች ምርጥ የሚባል ምግብ ነው።

ኮሮናቫይረስ በፓንጎሊኖች ላይ የተገኘ ሲሆን አንዳንዶች ቫይረሱ አሁን በሰዎች ላይ ከተገኘው ኮሮና ቫይረስ ጋር ከፍተኛ መመሳሰል አለው ይላሉ። ምናልባትም የሌሊት ወፍ ኮሮናቫይረስና ፓንጎሊኑ ኮሮናቫይረስና የዘር ቅንጣት ተለዋውጠው ይሆን?

ሳይንቲስቶች በችኮላ ድምዳሜ ላይ ላለመድረስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ነው። ከፓንጎሊን ጋር በተያያዘ ያለው ሙሉ ሳይንሳዊ መረጃም እስካሁን ይፋ አልተደረገም።

ኮሮናቫይረስ ላይ ምርምር እያደረጉ ያሉ ሳይንቲስቶች እንደሚያመለክቱት የፓንጎሊኖች የተለያዩ ዝርያዎችና እንዲሁም የሌሊት ወፎች የሚሸጡባቸው ገበያዎች ቫይረሱ ከአንዱ እንስሳ ወደ ሌላው ለመተላለፍ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህ ለቫይረሱ ወደ ሰዎች መተላለፍም እድል ይፈጥራል።

ኮሮናቫይረስ፡ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

ከኮሮናቫይረስ መቀስቀስ በኋላ የተዘጋው የዉሃኑ የእንስሳት ገበያም እንስሶች እዚያው ታርደው ስጋቸው የሚቀርብበት ነበር። በዚህ ገበያ ግመሎች እና ወፎችም ለእርድ ይቀርባሉ። በዚህ ገበያ ፓንጎሊን እና የሌሊት ወፍ ይሸጣሉ ባይባልም የቻይና ደህንነት ተቋም ግን ምን ዓይነት እንስሶች በገበያው እንደሚሸጡ መረጃ አለው።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ባለፉት ቅርብ ዓመታት የሰው ዘር የተዋወቃቸው ቫይረሶች ከዱር እንስሳት ወደ ሰዎች የተላለፉ ናቸው። በዚህ ረገድ ኢቦላን፣ ኤች አይ ቪን፣ ሳርስን እና የአሁኑን ኮሮናቫይረስ መጥቀስ ይቻላል።

የሰው ዘርን እንዲህ ላለፉ ቫይረሶች የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በሚገባ ማወቅ ከተቻለ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ያስረግጣሉ ተመራማሪዎቹ።