"እልም ያለ ሥርዓት አልበኝነት ሊፈጠር ይችላል" ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌ.)

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ Image copyright Ethiopian Citizens for Social Justice

ዛሬ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ ግጭቶችና ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የሰላም ዕጦት፣ ነገ ደግሞ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? የሚል ስጋት/ጭንቀት መኖሩን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።

ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የለውጡን ሂደት፣ በዚህ ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ የሚካሄደውን ምርጫ ፋይዳ እና በኢትዮጵያ ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በሚመለከት ባቀረቡት ግምገማና ጥሪ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የሠላም ዕጦት ኢዜማን እንደሚያሳስበው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።

ኢዜማ ከአባላቱና ከተለያዩ አካላት ያገኘውን መረጃ በመሰብሰብ፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ በመገምገም የጋራ አገራዊ ግንዛቤ ለመፍጠርና፣ ውይይት ለመክፈት በማለት በትናንትናው ዕለት አገራዊ ጥሪ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በመሪው በኩል አቅርቧል።

"በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም" ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ

ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት አገረ መንግሥት ግንባታ ያለፈችባቸውን ለውጦች ዘርዝረው፣ በእነዚህ ለውጦች ውስጥ የታዩት ተግዳሮቶች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት ይልቅ ማኅበረሰብን በጠባብ የዘውግ መለኪያ ብቻ የሚመለከት የአድሎ ሥርዓት መፍጠሩን በትንታኔያቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ለሦስተኛ ጊዜ ትልቅ የለውጥ ሂደት ውስት ገብታለች ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ "ነገር ግን ይህ ለውጥ ወደምንፈልገው የተረጋጋ ዲሞክራሲያዊ መንገድ ይውሰደን አይውሰደን ገና የታወቀ ነገር የለም" ሲሉ ይገልፃሉ።

ለዚህም እንደምክንያት ያነሱት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና ሥርዓት አልበኝነቶችን ሲሆን በሕዝቡ ዘንድም ቀጣዩ ምርጫ ያጫረውን ስጋት በዋቢነት ጠቅሰዋል።

ለውጥና የገጠመው ተግዳሮት

ፕሮፌሰር እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት ያለው ለውጥ የተጀመረው በፊት የነበረውን መዋቅር ሙሉ በሙሉ በማፈራረስ ሳይሆን ቀስ በቀስ የነበሩ ህፀጾችን እየቀነሱ ባለው መልካም ሁኔታ ላይ እየጨመሩ መሄድ በሚል መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ነገር ግን የተለያየ ዓላማ ይዘው ለለውጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች እና ለውጡን እንደግፋለን ብለው ወደ አገር ቤት የገቡ፣ በመንግሥትም ሆነ በተለያየ የሥልጣን እርከን ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ከለውጡ አላማ ውጪ መንቀሳቀስ የጀመሩት ወዲያውኑ መሆኑን ያነሳሉ።

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የኢዜማ መሪ ሆነው ተመረጡ

በዚህም የተነሳ ይላሉ ፕሮፌሰሩ ማዕከላዊው መንግሥት ሰላም የማስጠበቅ አቅሙን ከመገንባቱ በፊት ማኅበረሰቡ፣ በለውጡና በለውጡ ኃይሎች ተስፋ እንዲቆርጥ "መንግሥት የለም" ብሎ ሥርዓት አልበኝነት በአገሪቱ እየነገሰ ነው ብሎ እንዲሰጋና ለደህንነቱ ሲል ሁሉም ወደ ዘውጌ ምሽግ እንዲገባ እና የጣለውን ዘውጌ ሥርዓት እንዲናፍቅ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ።

ይህንን እንቅስቀሳሴ ሦስት አካላት ይሳተፉበታል በማለትም ሲዘረዝሯቸው የቀድሞ ሥርዓት ዋነኛ ተጠቃሚዎች፣ ለውጡን የሚፈልግና በባለተራ ዘውጌነት ክልሉን መግዛት የሚፈልግ፣ እንዲሁም የለውጥ ኃይሉን በፍፁም የማያምን ናቸው በማለት ያስቀምጧቸዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ከሆነ "ይህ ሦስተኛው ኃይል የለውጥ ኃይሉ በደንብ ከመደላደሉ በፊት በመቃወም፣ የህዝብ ተቀባይነት እንዳያገኝ በማድረግና ለውጡን ለማስኬድ ብቃትም ሆነ ተአማኒነት የለውም በማለት የተጀመረውን ለውጥ ከግቡ ለማድረስ ከሁሉም የተውጣጣ የሽግግር መንግሥት ይፈጠር በሚል የራሱን አጀንዳ ለማራመድ የሚሞክር ኃይል ነው።"

የሦስቱ ኃይሎች የጋራ ፍላጎት መንግሥትን ማዳከም ሲሆን በጋራ ላይሰሩ ይችላሉ ይላሉ።

አስፈሪው ስጋት

ፕሮፌሰሩ በዚሁ ጥሪ ባቀረቡበት ዘለግ ያለጽሑፍ ላይ እንዳስቀመጡት ሕዝቡ ይወክለኛል ያለውን ያለመሳቀቅ እና ፍርሃት መምረጥ ካልቻለ ባለፉት 18 ወራት ያየናቸውና ማኅበረሰባችንን ጭንቀት ውስጥ የከተቱት ችግሮች እጅግ በጣም በገዘፈ መልኩ የሚከሰቱበትና ወደ አጠቃላይ ቀውስ የምንገባበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ይሆናል ይላሉ።

ውክልናቸው በህዝብ ያልተረጋገጠላቸው "ወኪል ነን" ባይ ድርጅቶች "ውክልናቸውን ለማረጋገጥ" ሊሄዱበት የሚችሉት ብቸኛ መንገድ ጉልበትና አመጽ ብቻ ይሆናል ሲሉም ይገልጻሉ።

ይህ አመጽ ደግሞ አንድ ኃይል ወይም አንድ ወገን ብቻ የሚያካሂደው አመጽ ሳይሆን ሁሉም ሁሉንም የሚፈራበት፤ ሁሉም ከፍርሀቱ ለመውጣት ሳልቀደም ልቅደም በሚል ራሱን ለአመጽ የሚያዘጋጅበት፤ ተዘጋጅቶም "ጠላቴ" የሚለውን ኃይል ለማጥፋት የሚንቀሳቀስበት ነው።

የዘውጌ ክልሎች አንዱ ካንዱ ጋር ለውጊያ የሚነሳሱበት፣ በዘውጌ ክልሎችም ውስጥ፤ በየአካባቢው ባሉ 'ጊዜው የኛ ነው' ባይ ጉልበተኞች (የጦር አበጋዞች) የሚመሩ ቡድኖች የበላይነት ለማግኘት የዕርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ የሚገቡበት እልም ያለ ሥርዓት አልበኝነት የሚነግስበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

አክለውም ይህ የተያያዝነው የለውጥ ሂደት ከዚህ በፊት እንደነበሩት የለውጥ ሙከራዎች ከስሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሌሎች ማኅበረሰቦች የደረሱበት ስልጣኔ ሂደት አካል ከመሆን ይልቅ ከመቶዎች ዓመታት በፊት ወደነበርንበት የጨለማ ዘመን መልሶ የሚከተን ከሆነ አደጋው ወደኋላ መመለስ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር መቀጠል አለመቻልም ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ያለተማከለ አስተዳደር

ህዝብ በሚኖርበት የአስተዳደር እርከን ሁሉ እራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት የሚለውን መሰረተ ሃሳብ በግልጽ የሚቃወም የፖለቲካ ኃይል በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የለም የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ልዩነት ያለው ያልተማከለ ፌደራላዊ አስተዳደር ሲባል በተጨባጭ ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

አክለውም በፌደራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት ውስጥ ከታችኛው እርከን ጀምሮ ያሉ የመንግሥት አስተዳደሮች ሁሉ በአካባቢው ነዋሪ በተመረጡ መሪዎች ይተዳደራሉ ወይም አካባቢውን የሚመለከቱ አስተዳደራዊም ሆነ የልማት ውሳኔዎችን በህዝብ በተመረጡ መሪዎች ይወሰናሉ ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በብሔር የተደራጁ ኃይሎች ይህንን ለዘመናት "ታግለንለታል" የሚሉትን መርህ እንኳን በተግባር ለማዋል ፈቃደኞች አይደሉም" በማለት ከክልላቸው ውጪ ያሉ ዜጎች ምንም አይነት የዜግነት መብት የሌላቸው እንደሆኑ ተደርጎ የመቁጠር ሁኔታ እንዳለ ምሳሌ ጠቅሰው አስረድተዋል።

በማስከተልም "እንዲህ አይነት አስተሳሰብ በነገሰበት አገር ውስጥ የተለያየ የዘውግ ማንነት ያላቸው ህዝቦች አገራዊ አንድነት ፈጥረው በሰላም አብሮ መኖር ይችላሉ?" በማለት "ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሰርተውና ያፈሩትን ሃብትና ከሚኖሩበት አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ተጋብተው ወልደው የመሰረቱት ኑሮ ዋስትና ከሌለው እንዴት እራሳቸውን የዚህ አገር ዜጋ ነኝ ብለው ይጠራሉ?" ብለው ይጠይቃሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

ምርጫ 2012

ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የችግሮቻችን መፍቻ መነሻ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ምርጫው ተዓማኒ እንዲሆንና፣ የሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት መገለጫ እንዲታይ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮችን ይዘረዝራሉ።

ከእነዚህም መካከል አማራጭ አለን የሚሉ ድርጅቶች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው፣ ያለምንም ችግር ማኅበረሰቡን ሰብስበው ማናገር መቻል አለባቸው የሚለው ቀዳሚው ነው። መራጩም የሚፈልገውን ስለመረጠ ምንም ዓይነት የደህንንት አደጋ አይደርስብኝም ብሎ መተማመን ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ይላሉ።

በማስከተልም ሌሎች በምርጫው ወቅትና ከምርጫው በኋላ መሆን አለባቸው ያሏቸውን ከዘረዘሩ በኋላ ለምርጫው ሳንካዎች ናቸው ያሏቸውን ፓርቲያቸው በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የገጠሙትን ችግሮች በመንቀስ ያስረዳሉ።

ይህ ጉዳይ ከቀጠለ ለበለጠ ግጭት ሊዳርግና ምርጫውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋልም ብለዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተለይ በታችኛው እርከን ያሉ የመንግሥት አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች ከፖለቲካ ኃይሎችና ኢ-መደበኛ ከሆኑ የወጣት አደረጃጀቶች ጋር ህዝባዊ ስብሰባዎችን የማሰናከል፣ የተፎካካሪ ድርጅት አባሎችን ማሰርና ማንገላታት በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሮፌ. ብርሃኑ ለገዢው ፓርቲ ማስመረጫ ገንዘብ ማሰባሰብ በሚል እየተደረገ ነው በሚል በምሳሌ አስደግፈው ያቀረቡት ክስ ላይ "የመንግሥት ኃላፊነት ያለባቸው የገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊዎች የሚቆጣጠሩትን የንግድ ማህበረሰብ ለብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ እንዲያወጣ ሲጠይቁ፤ ባንዳንድ ቦታ የገቢዎች ባለስልጣን ማህተም ባለበት ደብዳቤ ነጋዴዎች ለብልጽግና ፓርቲ ገንዘብ እንዲያስገቡ ሲጠየቁ" እንደነበር አመልክተዋል።

"ይህ እየተሄደበት ያለው መንገድ የምርጫውን የመወዳደሪያ ሜዳ እጅጉን ሚዛናዊነት የጎደለው እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ከምርጫው በኋላ ሊመጣ የሚችለውን የሙስና አካሄድ የሚያሳይ ነውና ካሁኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል" በማለት የመግሥትና የፓርቲ ኃላፊነቶችን የሚያደበላልቁ ሁኔታዎች ማየታቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘም "የምርጫውን ተአማኒነት የሚያሳጡና ሀሳቦች በነጻነትና እንዳይንሸራሸሩ የሚያሰናክሉ ተግባራት፤ ወይም ምርጫው በፍትሃዊነት እንዳይካሄድና ወደ ገዥው ፓርቲ እንዲያደላ የመንግሥት ሃብትና መዋቅርን እራሱን ለማስመረጥ በሚል በየትኛውም መልክ ከተጠቀመበትና ምርጫው ተአማኒነት ካጣ፤ በሽግግሩ ሂደቶች ለሠራቸው ጥሩ ሥራዎች የምናመሰግነውን ያህል ዋናውን የመዳረሻ ሂደት ካበላሸው የለውጥ ኃይሉን በግልጽ ከመኮነንና ተጠያቂ ከማድረግ በፍጹም ወደኋላ እንልም!" ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ግን ይህ ምርጫ እውነትም የህዝብ ውክልና የሚገለጥበት እንዲሆን ከተፈለገ እነኝህን በየክልሉ በተለይም በታችኛው እርከን ላይ የሚገኙ የመንግሥት ጉልበተኞች በአስቸኳይ መቆጣጠር ካልተቻለ ይህ ምርጫ ከፍተኛ የተአማኒነት ችግር ውስጥ እንደሚገባ ግልጽ ነው በማለት ጠቁመዋል።

የጠቀሷቸው ችግሮች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነም የምርጫው አካሄድ ክፉኛ ሊያበላሽና "አስፈሪ" ወዳሉት ሥርዓት አልበኝነት ወይንም "አዲስ ዓይነት አምባገነናዊ ሥርዓት" አገሪቱን ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል።

አክለውም "ይህ የሽግግር ሂደት የለውጥ ኃይል እየተባለ ሲሞካሽ በነበረው ኃይል አጋዥነት ከተቀለበሰ የበለጠ ወደ አሳፋሪና አስፈሪ አደጋ አገራችንን መውሰዱ አይቀሬ ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ