የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያው አባ ብርሃነእየሱስ ጉዳይ መንግሥትን ማብራሪያ ጠየቀች

ካርዲናል ብርሃነየሱስ ደመረው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ እንዳይገቡ አሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የታገዱት የኢትዮጵያው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ጉዳይን በማስመልከት የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የኤርትራ መንግሥትን ማብራሪያ መጠየቋን ቫቲካን ኒውስ ዘገባ አለመለከተ።

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረበችው ለኤርትራው ብሔራዊ የሐይማኖት ጉዳዮች ቢሮ ነው።

ለቢሮው የቀረበው 'ማብራሪያ ይሰጠን' ደብዳቤ በኤርትራ የጳጳሳት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ አባ ተስፋጊዮርጊስ ክፍሎም የተፈረመ ነው።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ አሥመራ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የታገዱት ከሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ ሁለት አባቶች ጋር ነበር።

አባ ብርሃነእየሱስና አብረዋቸው የነበሩት አባቶች ወደ አሥመራ ያመሩት በኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ኪዳነምህረት ደብር በሚደረግ ትልቅ ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት እንደነበር ተገልጿል።

አባቶቹ ወደ አሥመራ እንዳይገቡ በአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መከልከላቸውን በማስመልከት ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ከታገዱት አባቶች አንዱ የነበሩት አባ ፍቅሬ ወልደትንሳኤ "ልዑኩ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሶ ማሟላት የሚገባውን ነገር ሁሉ አሟልቶ በተገቢው ሂደት አልፏል። መንገደኞች እንደደረሱ የሚሰጥ ቪዛም ለአንድ ወር ተብሎ ተሰጥቷል" ብለው ነበር።

ሁሉን ነገር ጨራርሰውና ቪዛቸውን ተቀብለው ከአውሮፕላን ማረፊያው ሊወጡ ሲሉ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የሚል ትዕዛዝ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መምጣቱ እንደተገለፀላቸውና ነገሮች በዚያ መልኩ እንደሄዱም አስረድተዋል አባ ፍቅሬ ወልደትንሳኤ።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አባቶች አሥመራ ከደረሱ በኋላ ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ በመከልከላቸው በአየር ማረፊያው ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት መጉላላታቸው ተነግሯል።