የተማሪዎቹ መታገት ከተሰማ 90 ቀናት አለፉ

የተጋች ቤተሰብ

ሕዳር 24፤ 2012 ዓ.ም. - ወላጆች ልጆቻቸው እንደታገቱ ሰሙ። ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ መኖሪያ ቀያቸው በማምራት ላይ የነበሩ ተማሪዎች ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ታገቱ።

ዜናው ቀስ በቀስ ሃገሪቱን ያዳርስ ጀመር። መረጃው የደረሰው ቢቢሲም የተማሪዎቹን ማንነት ማጣራት ያዘ። በዚህ መካከል ከአጋቾቿ ማምለጥ የቻለች አንዲት ተማሪ የተፈጠረውን አንድ በአንድ አስረዳች።

ተማሪ አስምራ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። «ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ። መጀመሪያ በአጋቾቹ የተያዝነው 18 ተማሪዎች ነበርን። እኔ ማምለጥ ስለቻልኩ አሁን ታግተው ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ወንዶች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው» ስትል ተናገረች።

ተማሪዋ አከጋቾቹ እንዴት እንዳመለጠችም ለቢቢሲ እንዲህ አስረዳች - «እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት። በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታተላለን' አሉኝ።»

ተማሪዎች መታገታቸው እንደተሰማ ስልክ የመታንላቸው የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ "ምንም አይነት መረጃ የለኝም። እኔ የሰማሁት ነገር የለም" ሲሉ ምላሽ ሰጡን። በዚያኑ ወቅት መረጃ ይኖራቸው እንደሆን የጠይቅናቸው የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው "ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም" ከማለት ውጪ ማብራሪያ መስጠት አልፈለጉም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተወሰኑ ተማሪዎች ቤተሰቦች ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ያክል ይደውሉላቸው እንደነበር ነገር ግን ያሉበትን አድራሻ እንደማያውቁት ያስረዳሉ።

የተማሪዎቹ መታገት ዜና ከአፅናፍ አፅናፍ ከተሰማ በኋላ የሀገር መነጋገሪያ ሆነ። ብዙዎች መንግሥት አንድ እንዲልና ታገቱ የተባሉ ተማሪዎችን እንዲያስለቅቅ አቤት አሉ። ይሁን እንጂ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች በጊዜ ምላሽ አልሰጠም። በዚህ መካከል ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሄዱ። ተማሪዎቹን አየሁ የሚል ጠፋ።

ጥር 02/2012

በዚህ መሃል ጥር 2/2012 በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣብያ የቀረቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል-አቀባይ አቶ ንጉስ ጥላሁን 'ከታገቱት ተማሪዎች መካከል 21 ተለቀዋል፤ የቀሩ አሉ፤ እነሱንም እናስለቅቃለን' ሲሉ መግለጫ ሰጡ። ተማሪዎቹን ያገታቸው ማነው? ከተለቀቁ የት ነው የሚገኙት? ከወላጆቻቸው ጋር ለምን እንዲገናኙ አልተደረገም? ለሚሉ እና ለሌሎች ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ አልነበረም።

ተማሪዎችን ታገቱ ከተባለ ከ50 ቀናት በኋላ የተወሰኑ ተማሪዎች ቤተሰቦች ወዳሉባት አዲስ ዘመን ከተማ ያቀናው የቢቢሲ ዘጋቢ ከተማዋ ሃዘን አጥልቶባታል ይላል። የታጋች ቤተሰቦች ፊታቸው ጠቁሮ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው ነው ያገኘኋቸው የሚለው ዘጋቢያችን ቤተሰቦችን ማነጋገር እጅግ አሳዛኝ እንደነበር ያስረዳል።

የምስሉ መግለጫ,

ወ/ሮ ማሬ አበበ የተማሪ በላይነሽ መኮንን ወላጅ

ተማሪዎች መታገታቸው ከተሰማ 50 ቀናት ካለፉ በኋላ መግለጫ የሰጡት በወቅቱ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ላቀ አያሌው ከታገቱ ተማሪዎች ወላጆች መካከል የተወሰኑትን አነጋግሬአለሁ ብለው ነበር። "እንደ አገር ተማሪዎችን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት አናሳ በመሆኑ ፈጥኖ መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውም ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም ሃገሪቱ ከገጠሟት ፈተናዎች አንዱ የተማሪዎች እገታ ነው ሲሉ መግለጫ ሰጡ። ይህንን የተማሪዎች ዕገታ ጉዳይ "በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ የተጨበጠ ውጤት ላይ ለማድረስ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን አሰባስቦ እየተረባረበ ነው" የሚል መግለጫ ከሰጡ ከወር በላይ ቢሆነውም ከመንግሥት የተሰማ ምንም አዲስ ነገር የለም እስካሁን።

እስከዛሬ ተማሪዎቹን ማን አገታቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ውል ያለው መረጃ ባይገኝም በርካታ መላ ምቶች ይሰጣሉ። ተማሪዎቹ ከታገቱ ሁለት ወራት በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጎ የነበረው በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የቀድሞ የኦነግ ጦር አዛዥ ዲሪባ ኩምሳ ወይም ጃል መሮ ተማሪዎቹ የታገቱት እሱ በሚመራው ቡድን እንደሆነ እንደሚነገር ተጠይቆ "ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ከእናንተ ነው። የትግል ዓላማችን ከተማሪዎች ጋር አይገናኝም። በተማሪዎቹ ላይም ይህን የተባለውን አይነት ተግባር አልፈጸምንም። እንደተለመደው የእኛን ስም ለማጉደፍ የተወራ ነው እንጂ በፍጽም እንዲህ አይነት ተግባር አሁንም ወደፊትም እንፈጽምም'' ሲል ማስተባበሉ አይዘነጋም።

ቢቢሲ ተማሪዎቹ መታገታቸው ከተሰማ ጀምሮ ያላቸውን መረጃ እንዲያካፍሉ የጠየቃቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት መረጃ እንደሌላቸው ከመናገር ውጭ ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።

90 ቀናት

የተማሪዎቹ መታገት ከተሰማበት ኅዳር 24 ጀምሮ እስከዛሬ የካቲት 12/2012 ባሉት 90 ቀናት የተማሪዎችን መታገት በተመለከተ በርካታ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎች ወጥተዋል።

ዜናው ከሃገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰምቷል። መንግሥት ስለ ጉዳዩ የተረጋገጠ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የወጡ መረጃዎች የተጣረሱ ይመስላሉ። የክልል አስተዳዳሪዎችም እርስ በርስ መወቃቀስ ይስተዋልባቸዋል።

የምስሉ መግለጫ,

መሪጌታ የኔነህ አዱኛ የተማሪ ግርማሽ የኔነህ አባት ናቸው።

መሪጌታ የኔነህ አዱኛ የተማሪ ግርማሽ የኔነህ አባት ናቸው። «ሞተውም ከሆነ እውነቱን ነግረውን ቤተሰብ ጋር ተሰባስበን አልቅሰን እርማችንን ብናወጣ ይሻለናል፤ እንዲህ በየቀኑ ምን ሆነው ይሆን እያልን በሰቆቃ ከምንኖር» ይላሉ።

ሌሎችም የተማሪ ቤተሰቦች በሰቀቀን ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ። ቀን አልፎ ቀን ቢመጣም የታገቱት ተማሪዎች አሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።

የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን ስለታገቱት ልጆች መጮህ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም ዘመቻውን መቀላቀላቸው አይዘነጋም። በተለይ ትዊተር በተሰኘው ማሕበራዊ መድረክ ላይ #Bringourgirlsback #Bringourstudentsback #WhereAreTheStudents? የተሰኙ ዘመቻዎች ተስተውለው ነበር።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታገቱት ተማሪዎች ጉዳይ የተዘነጋ መስሏል። አልፎ አልፎ ብልጭ ብልጭ ከሚሉ የማሕበራዊ ሚድያ ዘመቻዎች ውጭ ስለታገቱት ወጣቶች የሚያወራ እምብዛም አይስተዋልም። የተማሪዎቹ ወላጆች ለቅሶ ግን እንደቀጠለ ነው። ጥያቄው አሁንም አልተመለሰም - የታገቱት ተማሪዎች የት አሉ?