"በጫናም ሆነ በተፅእኖ የሚሆን ነገር የለም" አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
የምስሉ መግለጫ,

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ድርድር ስምምነት እንዲፈረም በከፍተኛ ሁኔታ ጫና እያደረገች ያለችው አሜሪካም ሆነ የዓለም ባንክ ሚና ሊፈታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል።

ይህ የተገለፀው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በዛሬው ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው።

የአሜሪካና የዓለም ባንክ ሚና ከታዛቢነት ያለፈ ነው ያሉት አቶ ገዱ "እነዚህ ወገኖች ከታዛቢነት አልፎ ሕግ አርቅቆ የማቅረብ ፍላጎት አላቸው" ብለዋል።

ከሰሞኑ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በውሃ የመሙላትና የሙከራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም እንዳለበት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ይህንንም አስመልክቶ አቶ ገዱ መግለጫው የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ችላ ያለና ስህተት ነው ብለውታል።

የአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ ያስተካክለዋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩት አቶ ገዱ "በፍፁም ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

በተለይም ሦስቱ አገራት እያደረጉት ያሉት ድርድር ጥሩ እመርታ እያሳየ ባለበት ወቅት በታዛቢነት ገብታ ሚናዋ የተቀየረው አሜሪካንም አውግዘዋል።

በአሜሪካ ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮች ላይ አገራቱ ልዩነታቸውን እያጠበቡና በርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ቢደረስም ከቴክኒክም ሆነ ከሕግ አኳያ ገና ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች አሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን በማይነካ መልኩ ከዲዛይን ጀምሮ ግድቡን እየገነባች መሆኑን አፅንኦት የሰጡት አቶ ገዱ ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር የምታደርጋቸውን ድርድሮች እንደምትቀጥልና በዚህም መልኩ እንደሚፈታም ተናግረዋል።

አሜሪካም ይህንን ታሳቢ በማድረግ አገራቱ በራሳቸው ወደ ስምምነት እንዲደርሱ የድርሻዋን ብቻ እንድትወጣ እና በግፊትም ሆነ በጫና ማንንም እንደማይጠቀም እና በሌላ ተፅዕኖ የሚሆን ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል።

አቶ ገዱ በግብፅም ሆነ በአሜሪካውያኑ በኩል ስምምነቱ ቶሎ እንዲፈረም ያላቸውን ፍላጎት ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ግን በበኩሏ ጊዜ ወስዳ ሕዝቡ ተሳትፎበት የሚወሰንና በድርድሩም ላይ በዋነኝነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚገባ መሆኑንም አሳውቀዋል።

የህዳሴው ግድብ የውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ድርድር ውጥረትና ውዝግብ በርትቶበታል ቢባልም ኢትዮጵያ ያላት ፅኑ አቋም በድርድር መፍታት ነው ብለዋል አቶ ገዱ በዛሬው መግለጫ።

በተለይም ከሰሞኑ ከግብፅ በኩል የሚሰማው ማስፈራሪያና ዛቻ "ጥቅም የለሽ፣ ለማንም የማይጠቅም እና ግንኙነትን ከማሻከር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ልትገነዘብ እንደሚገባ" አሳስበው ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የመገንባት ሙሉ መብት እንዳላት ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማንኛውንም አይነት ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበልም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, FANA BROADCASTING CORPORATE

የውሃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ከዘጠኝ አመት በፊት የተጀመረው የግድቡ ግንባታ ከብረት ሥራ፣ ከተርባይን ተከላ እና ከተቋራጮች አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ከነበሩበት ችግሮች ወጥቶ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተው 71 በመቶው ተጠናቋል ብለዋል።

በመጪው ሐምሌም ግድቡን ውሃ የመሙላት ሥራ እንደሚጀምር እቅድ እንዳለ ገልፀው፤ 4.9 ኪዩቢክ ሚሊሜትር የማመንጨት አቅምም አለው ብለዋል።

በዚህም እቅድ መሰረት በየካቲት እና መጋቢት ወር አካባቢ የሙከራ እንዲሁም ኃይል የማመንጨት ሥራ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

በሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የቆየው የህዳሴ ግድብ ድርድር ትኩረቱን ስቶ ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል ላይ መሄዱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ መናገራቸው የሚታወስ ነው።

እኚህ ምንጫችን ሱዳን የአቋም ለውጥ አድርጋ ከግብጽ ጋር መወገኗን እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ለግብጽ መወገናቸውን በመጠቆም አሁን ላይ ጉዳዩ "4 ለ 1" ሆኗል በማለት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በግድቡ ዙሪያ እጃቸውን እንዲያስገቡ መፈቀዱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ እንድትከፍል እያደረጋት እንደሆነ እኚህ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ውስጥ አዋቂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሰሞኑ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና ብሔራዊ ጥቅሟን የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማያደርግ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

የታላቁን የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሲደረግ ከነበረው ድርድር አንጻር ያወጣውን የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ተከትሎ ከፍተኛ ቅሬታ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መፈጠሩን ተገልጿል።

በአሜሪካ ዋሽንግትን ዲሲ ለሁለት ቀናት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

ሚኒስቴሩ የአሜሪካ መንግሥትና የአለም ባንክ በታዛቢነት በሚገኙበት የካቲት 19 እና 20/2012 ዓ. ም. ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ሊካሂድ በታቀደው ቀጣይ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ያስታወቀው፣ ተደራዳሪ ቡድኑ በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙርያ የሚያደርጉትን ድርድር የአሜሪካ መንግሥት ቀደሞ በታዛቢነት አሁን ደግሞ በአደራዳሪነት መግባቱን በመቃወም በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወቃል።