ኢራን በኮሮናቫይረስ ምክንያት 54ሺ እስረኞችን ፈታች

ኢራን እስረኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኢራን ዛሬ 54ሺ እስረኞችን ፈታለች። ዋናው ምክንያት ኮሮናቫይረስ ነው። ኢራን ባመነችው እስካሁን 77 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል። ሆኖም ቁጥሩ ከዚህ በሦስት እጥፍ ሊልቅ ይችላል የሚሉ መረጃዎች አሉ።

ኢራን እጅግ ተጨናንቀዋል በሚባሉ እስር ቤቶቿ በርካታ ዜጎች ታጉረዋል። ኮሮናቫይረስ ወደ እስር ቤት ቢዘልቅ ሺዎች እንደዋዛ ሊሞቱ ይችላሉ፤ ቫይረሱም ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል በሚል ነው እስረኞቹን ለመልቀቅ የወሰነችው።

የፍርድ ቤቶች አስተዳደር ቃል አቀባይ ጋላምሁሴን ኢስማኤሊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት እስረኞቹ ጊዜያዊ እረፍት ነው የተሰጣቸው። ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

ከደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተከሰው ከ5 ዓመት በላይ የተፈረደባቸው እስረኞች ግን ይህ ዕድል አይመለከታቸውም።

የብሪታኒያ ዜግነት ያላት የበጎ አድራጎት ሠራተኛ ናዛኒን ዘጋሪ ከሚፈቱት አንዷ እንደትሆን አንድ የእንግሊዝ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ተናግረዋል።

ሆኖም የርሷ ባለቤት ለጋዜጠኞች እንደተናገረው ቫይረሱ ይኑርባት አይኑርባት አልተመረመረችም። ይህ ሊሆን አይገባም ብሏል።

ኢራን የሞቱብኝ 77 ዜጎቼ ናቸው ብትልም የተጠቂዎች ቁጥር 2336 ደርሷል። እንዲያውም ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ ይችላል ተብሏል።

ኢራን በርካታ ባለሥልጣናቷ በቫይረሱ መጠቃታቸው ልዩ ያደርጋታል። ምክትል የጤና ሚኒስትሯ ብቻም ሳይሆን ሰሞኑን ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ የሕክምና ቡድን መሪ ፒርሆሴን ኮሊቫንድ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።