የሶሪያ ጦርነት፡ ቦንብ ሲፈነዳ የምትፈነድቀው ሶሪያዊት ሕፃን ቱርክ ገባች

ሳልዋና አባቷ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አባቷ ባለማመዳት መሠረት ቦንብ ሲፈንዳ የምትፈነድቀው ሶሪያዊት ሕፃን ከጦርነት ቀጣና ወጥታ ቱርክ መግባቷ ተሰማ።

ከቀናት በፊት በተሠራጨው ቪድዮ አማካይነት ታሪኳ በዓለም የናኘው ሳልዋ በቱርክ መንግሥት እርዳታ ወደ ድንበር አቋርጣ በጦርነት የታመሰች ሃገሯን ጥላ ሄዳለች።

በየደቂቃው ቦንብ በሚፈነዳባት ሶሪያ ልጁን የሚያሳድገው የሳልዋ አባት ልጁ ቦንብ በፈነዳ ቁጥር መሳቀቋን በመመልከት በሰቀቀን ፈንታ እንድትስቅ አለማምዷት ነበር። ሳልዋም የቦንብ ፍንዳታ በሰማች ቁጥር ትፈነድቃለች።

ኢድሊብ በተሰኘችው የጦርነት ቀጣና መኖሪያቸውን ያደረጉት ሳልዋና አባቷ ከቀናት በፊት በተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስላቸው ምክንያት ታዋቂ ሆነዋል። ቪድዮው በተለቀቀ በሳምንቱ የቱርክ ባለሥልጣናት ሕፃኗ ኢድሊብን ለቃ እንድትወጣ አድርገዋል።

ኢድሊብ በመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች የተያዘች የመጨረሻ ግዛት ናት። በቱርክ የሚታገዙት አማፂያንና የመንግሥት ኃይሎች የሞት ሽረት ትግል እያደረጉባትም ይገኛል።

ከታኅሣሥ ጀምሮ ባሉት ጥቂት ወራት ብቻ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሶሪያዊያን ወደ ቱርክ ድንበር ተሰደዋል።

ሳልዋና አባቷ አብዱላህ ሞሐመድ የጦርነትን ሰቀቀን ለየት ባለ መልኩ ለመወጣት መሞከራቸው ብዙዎችን ከንፈር አስመጥጦ ነበር።

አብዱላህ ለሳልዋ በሌላው ዓለም ሕፃናት ርችት [ፋየርወርክ] ሲፈንዳ ሲያዩና ሲፈነደቁ በማሳየት ነው ቦንብ ሲፈንዳ እንድትስቅ አድርጎ ያለማዳደት።

አባትና ልጅ ወደ ቱርክ ከገቡ በኋላ ደቡብ ቱርክ ውስጥ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ መወሰዳቸውም ተሰምቷል።

ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ባልደረባ የሳልዋና አባቷን ፎቶ በትዊተር ገፁ ለመላው ዓለም አጋርቷል።

የሳልዋ አባት ልጁ ወደ ቱርክ መግባቷ እንዳስደሰተው ገልፆ ሳልዋ ወደ ትምህርት ቤት ገብታ እስክትማር እንደቸኮለ ተናግሯል።

ቱርክ ውስጥ 3.7 ሚሊዮን ገደማ ሶሪያውያን ስደተኞች አሉ።