በጎንደር ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ሲያከፋፍሉ ነበር የተባሉ 13 ካናዳዊያን በዋስ ተለቀቁ

መድሃኒት

የፎቶው ባለመብት, DON EMMERT

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ሲያከፋፍሉ ነበሩ የተባሉ 13 ካናዳዊያን እና ሁለት ኢትዮጵያዊያን እያንዳንዳቸው በ20ሺህ ብር ዋስ መለቀቃቸውን በጎንደር የሦስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ደሳለኝ አበራ ለቢቢሲ ገለጹ።

15ቱ ግለሰቦች ትላንት የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ. ም. በዋስ እንደተለቀቁ ገልጸዋል።

15ቱ ግለሰቦች ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 አካባቢ በሚገኝ ትምህርት ቤት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች በመስጠት ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታከለው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት መድሃኒት የተሰጣቸው ሰዎች እና ትምህርት ቤቱ በሰጡት ጥቆማ ነው ተብሏል።

"ጥቆማውን መነሻ አድርገን የህክምና ባለሙያዎች እንዲያዩት እና እንዲያረጋግጡ አድርገናል። በትክክልም ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ለተማሪዎቹ እየሰጡ መሆኑን ካረጋገጥን በኋላ ሰዎቹን በቁጥጥር ስር አውለናል" ሲሉ ኮማንደር አየልኝ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በርካታ መድኃኒቶች ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው ያሉት ኮማንደር አየልኝ፤ "እነዚህ መድኃኒቶች እስከ ስድስት ዓመት ድረስ ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው" ብለዋል።

"ከዚህ በፊት በዋነኛነት እርዳታ የሚሰጡት አልባሳት እና የተለያዩ ነገሮችን ነበር። አመጣጣቸውም ይሄን ብለው ነው። ነገር ግን በተጨማሪ ይሄን ድርጊት አከናውነዋል" ሲሉም አክለዋል።

ኮማንደር አየልኝ እንደተናገሩት፤ ተጠርጣሪዎቹ ተማሪዎቹ በሚነግሯቸው የህመም ምልክቶች እና 'እንዲህ ዓይነት ህመም አለብን' ሲሏቸው ያለምንም መመርመሪያ መሣሪያ እና ቴክኖሎጂ መድኃኒት ሰጥተዋል ተብሏል።

መድኃኒቶቹን ወስደው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ሲጠየቁም "መድኃኒቱን የወሰዱ ሰዎችን የጤና ሁኔታ ምርመራ ማድረግ ያስፍልጋል። አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳት ላይኖር ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። እሱን ሙያተኛ የሚያስቀምጠው ይሆናል" ሲሉ መልሰዋል።