የአሜሪካ ግዙፍ ግዛት ካሊፎርኒያ በኮሮናቫይረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች

Woman with face mask

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በካሊፎርኒያ ግዛት አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ መሞቱን ተከትሎ በግዛቲቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። በካሊፎርኒያ የተመዘገበው ሞት በአጠቃላይ በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተመዘገበውን ሞት ወደ አስራ አንድ ከፍ አድርጎታል።

ከአስራ አንዱ አስሩ ሞቶች የተመዘገቡት በዋሽንግተን ግዛት ሲሆን ቴክሳስና ኔብራስካም የቫይረሱ ወላፈን ደርሷቸዋል ተብሏል።

ትናንት ረቡዕ በመላ አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ ይቻል ዘንድ አሰራሮች ተዘርግተዋል። በዓሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ ቢያንስ 150 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ህክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በ16 የአሜሪካ ግዛቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።

ዋሽንግተን እና ፍሎሪዳ ግዛቶችም ቫይረሱን ለመከላከል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጁ ቀናት ተቆጥረዋል።

በካሊፎርኒያ በኮሮናቫይረስ የሞቱት የ71 ዓመት አዛውንት ባለፈው የፈረንጆቹ ወር በመርከብ ከሳንፍራንሲስኮ ሜክሲኮን ለመጎብኘት ሄደው የነበሩ ናቸው።

ይህ መርከብ በሌላ ጉዞ በርካቶችን አሳፍሮ ጃፓን ወደብ ላይ እንዲቆም ተገድዶ የነበረ ሲሆን ከተሳፋሪዎቹ ብዙዎቹ ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።

በአሜሪካ ብዙ የኮሮናቫይረስ ኬዞች ሊመዘገቡ ይችላል በማለት በማስጠንቀቅ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች አሉ።

እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ 92 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን 80 ሺህ የሚሆኑት ኬዞዎች የተመዘገቡት ቻይና ውስጥ ነው።

በሌላ በኩል ሶስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን በተመሳሳይ ብዙዎቹ ሞቶች የተመዘገቡት በቻይና ነው።

በሌላ በኩል ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቆጣጠር ይችሉ ዘንድ በቫይረሱ ለተጠቁ አገራት 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በትናንትናው እለትም ዓለም ባንክ ተመሳሳይ እርዳታ እንደሚያደርግ ያስታወቀ ሲሆን የተቋማቱ ውሳኔ የመጣው ቫይረሱ ከቻይና ውጭ በ70 አገራት መሰራጨቱን ተከትሎ ነው።