'ኮሮናቫይረስ አለብህ' በሚል ቡጢ የቀመሰው የኦክስፎርድ ተማሪ

በቡጢ የተነረተው ጆናታን ቀዶ ጥገና ያስፈልገኛል ብሏል

የፎቶው ባለመብት, JONATHAN MOK

የምስሉ መግለጫ,

በቡጢ የተነረተው ጆናታን ቀዶ ጥገና ያስፈልገኛል ብሏል

ኢሲያዊያን ከዚህ ኮሮናቫይረስ ወዲህ በየአካባቢው መገለል እየደረሰባቸው ነው። በቅርቡ በትዊተር የተሰራጨ አጭር ቪዲዮ 'ኮሮናዎች መጡ" በሚል ቻይናዎች በኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ሰዎች ሲሸሽዋቸው ያሳይ ነበር።

አሁን ደግሞ በእንግሊዝ ሎንዶን በጎብኚዎች በሚዘወተረው የኦክስፎርድ ጎዳና አንድ የ23 ዓመት ወጣት ከበድ ያለ ድበደባ ደርሶበታል።

ጆናታን ሞክ አደጋው የደረሰበት በምሽት ወደ ቤቱ እየሄደ ነው። 4 ወጣቶች "ቁም! ኮሮና አለብህ" በሚል ፊቱ እስኪያባብጥ ደብድበውታል።

ጆናታን ሞክ ትውልዱ ከሲንጋፖር ነው። ከአራቱ ደብዳቢዎቹ ሁለቱ ገና የ16 እና 15 ዓመት ልጆች ሲሆኑ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ካደረገ በኋላ ለቋቸዋል።

ጆናታን ሞክ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን ተማሪ ነው። የተደበደበውም በቶተንሃም ኮርት ሮድ አጠገብ ነው።

እሱ እንደሚለው መጀመርያ የደበደበው ሰው 'ሲያየኝ በጣም ተናዶ ነበር' ይላል። እየደበደበኝ ጮክ ብሎ "ያንተን ኮሮናቫይረስ ወደ አገሬ እንዲገባ አልፈልግም፤ ውጣልን" ሲል ይጮኽ ነበር ብሏል።

ሁለተኛው ደብዳቢም በቡጢ አፍንጫዬን ነርቶኛል።

ጆናታን ሞክ ለቢቢሲ እንደተናገረው ቀኝ ዐይኑ ሥር ያለ አጥንት በድብደባው በመሰበሩ በቅርቡ ቀዶ ጥገና ያደርጋል።

ኮሮናቫይረስ ተነስቶባታል ተብላ የምትገመተው ሁቤ ግዛት፣ ውሃን ከተማ በቻይና የምትገኝ በመሆኑ በመልካቸው ቻይናዊያንን የሚቀርቡ ኢሲያዊያን በተቀረው ዓለም ለተለያዩ መገለል፣ መንጓጠጥና ጥቃት እየተዳረጉ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ይህ ዜና እስኪዘገብበት ሰዓት ድረስ በመላው ዓለም 100ሺ 598 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። 3410 ሰዎች ሞተዋል። 55ሺ 991 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።