'ፌክ' ፓስፖርት ይዞ ተገኝቷል የተባለው ሮናልዲንሆ ፍርድ ቤት ቀረበ

ሮናልዲንሆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብራዚላዊ የእግር ኳስ ጠቢብ ሮናልዲንሆና ወንድሙ ፓራጓይ ለመግባት ሃሰተኛ ፓስፖርት ተጠቅመዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

አቃቤ ሕግ፤ ወንድማማቾቹ ባለፈው ረቡዕ የፓራጓይ ዋና ከተማ አሱንሲዮን ሲደርሱ ሃሰተኛ ሰንዶች ተሰጥቷቸዋል ሲል ይከሳል።

አቃቤ ሕግ ወንድማማቾቹ ቀለል ያለ ቅጣት ይቀጡ የሚል ሃሳብ ቢያቀርብም ዳኛው ግን የኋሊት ጠፍራችሁ አምጡልኝ ሲሉ አዘዋል። ሮናልዲንሆና ወንድሙ አርብ ዕለት ነው የካቴና ሲሳይ የሆኑት።

አቃቤ ሕግ ሮናልዲንሆና ወንድሙ በቀጣፊዎች ተታለዋል ይላል። ወንድማማቾቹም 'እኛ የምናውቀው ነገር የለም' ይላሉ።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ያረፉበትን ሆቴል ከበረበረ በኋላ ምርመራ አድርጎባቸዋል። ሮናልዲሆንና ወንድሙ 'ፖስፖርቱ ሲሰጠን የክብር መገለጫ መስሎን ነበር' ይላሉ።

ፓርጓዊው ዳኛ ሮናልዲንሆም ሆነ ወንድሙ ፍርድ እስኪሰጣቸው ድረስ ማቆያ እንዲሰነብቱ አዘዋል።

ዓለም ካየቻቸው ድንቅ እግር ኳሰኞች አንዱ የሚባለው ሮናልዲንሆ ባለፈው ሐምሌ ግብር አልከፈለም ተብሎ የብራዚልና የስፔን ፓስፖርቱን መነጠቁ አይዘነጋም። አልፎም ብራዚል ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የተፈጥሮ ሃብት መጠበቂያ ሥፍራ ገንብቷል ተብሎ ክስ ቀርቦበት ነበር።

«ቃዋቂ እግር ኳሰኛ ነው። አከብረዋለሁ። ነገር ግን ሕግ ሕግ ነው» ሲሉ የፓራጓይ ሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ለሃገራቸው ጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የ39 ዓመቱ ሮናልዲንሆ ወደ ፓራጓይ ያቀናው አዲስ የታተመ መፅሐፉን ለማስተዋወቅና እርዳታ ለሚሹ ሕፃናት ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው።

ሁለት ጊዜ የዓለም ኮከብ ተብሎ የተሸለመው ሮናልዶ የ2002 ዓለም ዋንጫ አሸናፊ ነው። አልፎም ከባርሴሎና ጋር ስኬታማ ጊዜ አሳልፏል።

ብራዚላዊው የኳስ ቀማሪ 100 ሚሊዮን ፓውንድ የተጣራ ሃብት እንዳለው ይገመታል።