በኮሮናቫይረስ ተያዙ ከተባሉት ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነጻ ሆነ

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባሳለፍነው አርብ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኮሮናቫይረስ ተያዙ ከተባሉ የተለያዩ አገራት ዜጎች መካከል ሁለቱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።

ይህንኑ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአቡዳቢ የአምባሳደሩ ተወካይ ወ/ሮ ኑሪያ መሐመድ "እኛም እንደናንተው በሚዲያ ከመስማት ውጭ ምንም መረጃው የለንም" ማለታቸው ይታወሳል።

አክለውም ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ኦፊሴሊያዊ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያውያኑ የጤናና ሌሎች ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ አዲስ መረጃ አግኝታችሁ ይሆን ስንል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚኒስትር ዲኤታ ለሆኑት ሊያ ታደሰ ጥያቄ አቅርበንላቸዋል።

እሳቸውም ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ነዋሪነታቸውን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ያደረጉ መሆናቸውን በማረጋገጥ አንደኛው ግለሰብ በንጉሱ የግል አውሮፕላን ውስጥ የሚሰራ የበረራ ባለሙያ መሆኑን ነግረውናል።

'' ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንደኛው ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ መረጋገጡን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጤና ሚኒስቴር አረጋግጠናል፤ ሁለተኛው ታማሚ ግን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ዝርዝር መረጃ አልሰጡንም። ነገር ግን አሳሳቢ የሚባል ነገር እንዳልሆነ ገልጸውልናል።''

ሚኒስትር ዴኤታዋ የአንደኛው ኢትዮጵያዊ ሁኔታ ከባድ የሚባል አይደለም ማለት '' በሽታው ልክ እንደ ጉንፋን አይነት በሽታ እንደመሆኑ አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ልክ እንደማንኛውም ጉንፋን ታማሚ ነው የሚሆኑት። ነገር ግን አንዳንዶች በሽታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያድግባቸዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ጉንፋን ብቻ በሚባል ደረጃ ላይ ነው ያለው ማለት ነው'' ብለዋል።

ስለዚህ አንደኛው ኢትዮጵያዊ ከህመሙ የማገገም እድሉ እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለዋል። ከቫይረሱ ነጻ እንደሆነ የተነገረው ግለሰብ ግን በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲሆን የሚያስገድደው ነገር እንደሌለና ወደ ቀድሞ ህይወቱ መመለስ እንደሚችልም ታውቋል ሲሉ አክለዋል።

ከግለሰቦቹ ማንነት ጋር በተያያዘ አንደኛው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ሰራተኛ ሲሆን ሁለተኛው ግን ኢትዮጵያዊ ከመሆኑና ነዋሪ ከመሆኑ ውጪ ሌላ መረጃ አለማግኘታቸውንም ነግረውናል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ 93 አገራት ቫይረሱ እንደተገኘ መገለጹን ተከትሎ ምናልባት በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለበሽታው ተጋልጠው እንደሆነ መረጃው አላችሁ ስንልም ለሚኒስትር ዴኤታዋ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር።

እሳቸውም '' እስካሁን ምንም የደረሰን መረጃ የለም። በየአገራቱ የሚገኙ ኤምባሲዎች ችግር ካለ ይነግሩናል፤ የጤና አታሼዎችም ይህንን በተመለከተ መረጃ ያደርሱናል። ነገር ግን ከበሽታው ጋር በተያያዘ እስካሁን ከየትኛውም ኤምባሲ መረጃ አልደረሰንም'' ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of health and prevention/FB

ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላልና በቂ ምርመራ ለማድረግ ያላት ዝግጁነት ምን እንደሚመስልም ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲለመልሱም ''በላብራቶሪ ምርምራ በኩል ሙሉ ለሙሉ አገር ውስጥ እየሰራን ነው። ምናልባት የሚፈጠረው አይታወቅምና ተጨማሪ ለምርመራ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለማግኘትም ጥረት እየተደረገ ነው። ነገር ግን በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ምርመራዎችን ለማድረግ በቂ አቅም አለን'' ሲሉ ኢትዮጵያ ያላትን ዝግጁነት አብራርተዋል።

ከአፍ መሸፈኛ 'ማስክ' ጋር ተያያዘም ለህብረተሰቡ ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ነገር አለ በማለት '' ይህንን በሽታ ለመከላከል ሁሉም ሰው ማስክ ማድረግ አያስፈልገውም፤" ካሉ በኋላ የአፍ መሸፈኛ 'ማስክ' እንዲያደርጉ የሚመከሩት የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ገልፀው ይህም ወደሌሎች ሰዎች እንዳያስተላልፉ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ አለማቆሙን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስጋታቸውን እየገለጹ እንደሆነና የበሽታውን የመዛመት እድል ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም በሰፊው እየተዘገበ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በሽታውን ለመቆጣጠር ምን እያደረገ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

'' አሁን ትልቁ ስጋት ቻይና አይደለም፤ በቀን በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ቀንሷል። በአሁኑ ሰአት ብዙ ሰዎች እየተያዙ ያሉት ቻይና ሳይሆን በተለያዩ አገራት ነው፤ በተለይ ደግሞ እሲያና አውሮፓ። በአፍሪካም በስምንት አገራት ውስጥ ተገኝቷል።''

አክለውም ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዳለ ሆኖ የክትትል ስራው ግን ማለትም ለ 14 ቀናት የሚቆየው የሚከናወነው ከቻይና በመጡ መንገደኞች ላይ ብቻ ነበር ብለዋል።

አሁን ግን ከ 7 አገራት የሚገቡ መንገደኞች ላይ ክትትል እንደሚደረግ ገልፀው፤ አምስቱ ከፍተኛ የታማሚ ቁጥር የተመዘገበባቸው ሲሆን ሁለቱ ደግሞ መንደገኞች በብዛት እንደ ትራንዚት የሚጠቀሟቸው አገራት ናቸው ብለዋል።

"ከነዚህ አገራት የሚመጡትን መንገደኞች እየመረመርን የሚጠረጠሩትን ለ 14 ቀናት ክትትል እናደርግባቸዋለን።''

ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚገኙና እንደ ሳንባ ኢንፌክሽን አይነት በሽታዎች ያጠቋቸው ታማሚዎችን የመመርመር ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ሚኒስትር ዴኤታዋ ጨምረው ተናግረዋል።