ኮሮናቫይረስ፡ ጣልያን 60 ሚሊየን ሕዝቧ በር ዘግቶ እንዲቀመጥ አዘዘች

ኮሎሲየም ጣልያን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየተፋጠነባት ባለችው ጣልያን መንግሥት በመላ አገሪቱ ጉዞዎች እንዳይደረጉ፤ ምንም ዓይነት ስብሰባዎችም እንዳይካሄዱ ትእዛዝ ገደብ ጥሏል።

ትናንት የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጣልያናዊያን ቤታቸው እንዲቀመጡና የግድ አስፈላጊ ነው የሚሉት ጉዞ ካላቸው ደግሞ የመንግሥትን ፍቃድ እንዲጠይቁ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

እርምጃው የተወሰደው በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ እንደሆነ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ባደረጉት ንግግራቸው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ምንም ጊዜ የለም" በማለት ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ አስረድተዋል።

በትናንትናው እለት በጣልያን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ366 ወደ በከፍተኛ ደረጃ ወደ 463 ጨምሯል።

ይህ ደግሞ ቫይረሱ ከተቀሰቀሰባት ቻይና ቀጥሎ ጣልያንን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ የተጎዳች አገር አድርጓታል።

የጣልያን መንግሥት ከትናንት በስቲያ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በ24 በመቶ የጨመረ ሲሆን በ20 ዎቹም የጣልያን ክልሎች ቫይረሱ ተሰራጭቷል።

"በቫይረሱ የሚያዙም የሚሞቱም ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው። እገዳዎች እንዲጠነክሩ ውሳኔ ያስተላለፍኩትም ለዚሁ ነው። ለጣልያን ስንል ሁላችንም የሚበጀውን ማድረግ አለብን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ ዜጎች ማድረግ ያለባቸው ተገቢ ነገር ከቤታቸው አለመውጣት እንደሆነ ገልፀዋል።

የጣልያን መንግሥት እንዳለው ለመንቀሳቀስ የሚፈቀድላቸው አሳማኝ የስራና የቤተሰብ ምክንያት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሲሆን ከጣልያን የሚወጡም ሆኑ የሚገቡ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የጉዞ ምክንያታቸውን ማስረዳት ግድ ይላቸዋል።

የባቡር ተጓዦችም የሙቀት መጠን የሚለካ ሲሆን በጣልያን የተለያዩ የባህር ዳርቻዎች መርከቦች እንዳያርፉም እገዳ ተጥሏል።