ዚምባብዌ ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ወላጆችን ልታስር ነው

እአአ በ1984 ተማሪዎች በዚምባብዌ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዚምባብዌ መንግሥት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ እና ልጆቻቸው ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ወላጆችን ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ እንደሆነ አስታወቀ።

መንግሥት እስከ 16 ዓመት እድሜ ድረስ ትምህርት ግዴታ እንዲሆን ያደረገው በአገሪቱ ትምሀርት የሚያቋርጡ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለመጣ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች 20 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም።

አሁን መንግሥት ያወጣው ህግ ተማሪዎች የትምህርት ክፍያ ባለመክፈላቸው ወይም እርጉዝ በመሆናቸው ማባረርንም ጭምር እንደ ጥፋት ቆጥሮ ይቀጣል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ባለፈው ዓመት 60 በመቶ የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ክፍያ አልፈፀማችሁም በሚል ከትምህርት ቤት ተባርረው ነበር።

ባለፈው ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ሮበርት ሙጋቤ አገሪቷ ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ በዘረጉት የትምሀርት ስርዓት አድናቆትን አግኝተው ነበር።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የህዝብ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ሙጋቤ የዘረጉት የትምህርት ስርዓት ለጥቁር ዚምባብዌያን ትልቅ የትምህርት እድል ፈጥሮ ነበር።

በዚህም ዚምባብዌ ከአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ሽፋን ያላት አገር ሆና ነበር።

ነገር ግን ነፃ ትምህርት በ1990ዎቹ እንዲቆም የተደረገ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ በነበሩት ዐሰርታት የአገሪቱ የትምህርት ስርዓት መፈራረስ ጀመረ።

መንግሥት ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ወላጆችን ለመቅጣት የተገደደው በዚህ መልኩ የወደቀውን የአገሪቱ ትምህርት ለመታደግ በማሰብ ነው።

ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ወላጆች የሁለት ዓመት እስር ወይም የ260 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

መንግሥት ራሱ ቃል የገባውን የነፃ የትምህርት እድል ማሟላት ሲያቅተው የዚህ ዓይነት ህግ ማውጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልፁ አሉ።

እርግዝና፣ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የትምሀርት ቤቶች ተደራሽ አለመሆን፣ የትምህርት ፍላጎት አለመኖር በአገሪቱ እየታየ ላለው የትምሀርት ማቋረጥ በምክንያትነት የሚቀመጡ ናቸው።