የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ አንሺ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ሰር ሞሂንድራ ዲሎን

የፎቶው ባለመብት, Mohinder Dhillon

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ፎቶ ግራፍ አንሺ በመሆን ያገለገሉት ሰር ሞሂንድራ ዲሎን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ሞሂንድራ በአፄ ኃይለሥላሴ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ አብረዋቸው በመጓዝ ምስሎችን ያስቀሩ እንደነበር በህይወት ድርሳናቸው ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

የ85 ዓመቱ ሞሂንድራ የ1977ቱን የኢትዮጵያ ድርቅ በምስል በማስቀረትም ይታወቃሉ።

ሞሂንድራ በሙያቸው ስማቸውን የተከሉበትና አሻራውን ያኖሩበት ይህ ስራቸው መሆኑን የሚናገሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ረሃቡ በተከሰተበት ገጠራማ አካባቢዎች ለ13 ወራት በመቀመጥ ዕለት በዕለት በረሃብ የተጎዱ ጨቅላ ሕፃናት ዓይናቸው ስር ሲሞቱ መመልከታቸው በአንድ ወቅት ገልፀው ነበር።

ሞሂንዲራ ከመሐመድ አሚን ጋር በመሆን የቀረፁትና 'አፍሪካን ካላቫሪ' በሚል ርዕስ የተሰራው የ30 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ረሃብ ለዓለም ሕዝብ በማሳየት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ከዚህ ዘጋቢ ፊልም ተከትሎ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተለያዩ እርዳታዎችን በመጫን ወደ ኢትዮጵያ ያመሩ ሲሆን እማሆይ ቴሬሳን የመሰሉ ታላላቅ ሰዎች ፊልሙ ያሳደረባቸውን ስሜት ገልፀው ነበር።

ሞሂንድራ፣ እማሆይ ቴሬሳ እጃቸውን ይዘው " ልጄ፣ ፈጣሪ ይህንን ፊልም አንድትቀርጸው መርጦሃል" እንዳሏቸው በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Mohinder Dhillon

ሞሂንድራ ለአፄ ኃይለሥላሴና ለኢትዮጵያ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በልጅ ልጃቸው ዘረያዕቆብ አስፋወሰን ኃይለስላሴ በኩል "ናይት ኮማንደር" የሚል ዕውቅና ተቀብለዋል።

ራሳቸውን በራሳቸው የፎቶግራፍ ማንሳት ጥበብን ማስተማራቸውን የሚናገሩት ሞሂንድራ፣ ከአጼ ኃይለስላሴ ሌላ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬኒያታ፣ የኡጋንዳውን ኢዲያምን ዳዳ፣ ሮበርት ሙጋቤ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎችን እንቅስቃሴ በምስል ማስቀረት ችለዋል።

ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር መስራት በጀመርኩበት ወቅት " የአፍሪካ መሪ" ተደርገው ይታሰቡ ነበር የሚሉት ሰር ሞሂንድራ፣ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ረሃብ የነበራቸውን ሞገስና ተቀባይነት እንደጎዳው በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ተናግረዋል።

ሰር ሞሂንድራ ዲሎን የተወለዱት በሕንድ ፑንጃብ በምትገኝ አነስተኛ መንደር ሲሆን መብራት፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም መፀዳጃ በሌለበት ቤት ውስጥ ልጅነታቸውን እንዳሳለፉ ተናግረዋል።