ኮሮናቫይረስ፡ የኮሮናቫይረስ መድሃኒትን ወይም ክትባቱን ለማግኘት ሳይንቲስቶች ምን ያክል ተቃርበዋል?

በምርምር ላይ ያሉ ሳይንቲስት Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በምርምር ላይ ያሉ ሳይንቲስት

የኮሮናቫይረስ መድሃኒን ወይም ክትባቱን ለማግኘት ሳይንቲስቶች የሚደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ኮሮናቫይረስ በመላው ዓለም እየተስፋፋ ቢሆንም ወረርሽኙን የሚያስቆም ክትባትም ሆነ መድሃኒት እስካሁን አልተገኘም።

በመሆኑም ሕይወትን ለመታደግ የሚያስችለውን መድሃኒት ለማግኘት ምን እየተሰራ ነው? የሚለውን ጥያቄ በወረርሽኙ የሚሰቃዩም ጭንቀት የሆነባቸው ሰዎችም ይጠይቃሉ።

የቫይረሱን ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት ምርምሮች በአይን እርግብግቢት ፍጥነት እየተከናወኑ ነው። 20 የሚደርሱ ክትባቶች በሂደት ላይ ናቸው። አንደኛው ክትባት እስከ ዛሬ ባልተለመደ መልኩ ከእንስሳት ላይ ሳይሞከር በቀጥታ በሰው ላይ ተሞክሯል።

ሌሎች ሳይንቲስቶች ደግሞ እንስሳት ላይ እየሞከሩ ሲሆን በዚህ ዓመት መጨረሻ በሰው ላይ ይሞክራሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

በእርግጥ ሳይንቲስቶች ተሳክቶላቸው ክትባቱን በዚህ ዓመት መስራት ቢችሉ እንኳን የተገኘውን ክትባት ለመላው ዓለም በሚበቃ መልኩ አምርቶ የማቅረብ ቀሪ ብዙ ሥራ ይኖርባቸዋል። ይህም ማለት ቢያንስ እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ድረስ ክትባቱ ላይደርስ ይችላል ማለት ነው።

ሁሉም ነገር ባልተጠበቀ ፍጥነት እየተከናወነ ያለ ተግባር ነው። በዚህ ፍጥነት ደግሞ ምንም እክል እንደማያጋጥም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

በአሁኑ ወቅት በሰው ላይ እየተስፋፉ ያሉት አራት የኮሮናቫይረስ አይነቶች ናቸው። ሁሉም ጉንፋንን ያስከትላሉ። ለዚህ ደግሞ ምንም ክትባት አልተዘጋጀም።

ክትባቱ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችን ሊታደግ ይችላል?

በትልልቅ ሰዎች ላይ የሚኖረው ፈዋሽነት ያን ያክል ላይሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ይህ ደግሞ የክትባቱ ችግር ሳይሆን በእድሜያቸው የገፉ ሰዎች ያሏቸው በሽታን የሚከላከሉ ሕዋሳት በፍጥነት በሽታን ለመከላከል መልስ አይሰጡም። ይህ ደግሞ በየዓመቱ በተለያዩ ወረርሽኞች ላይ ተሞክሮ የተረጋገጠ ነው።

የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረው ይሆን?

ሁሉም መድሃኒቶች የህመም ማስታገሻን ጨምሮ የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ነገር ግን አንድ በሂደት ላይ የሚገኝ ክትባት ምን ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ማረጋገጥ የሚቻለው በክሊኒካል ሙከራ ነው። ይህ ደግሞ ጥብቅ ክትትል የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው።

ክትባቱን ሊያገኝ የሚችለው ማን ነው?

ክትባቱ ከተገኘ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የክትባቱ ስርጭት የተገደበ ይሆናል። ከዚያም ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ለማን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይወሰናል ማለት ነው። ኮቪድ-19ን [ኮሮናቫይረስን] ከፊት ሆነው የሚዋጉት የሕክምና ሞያተኞች የመጀመሪያዎቹ የክትባቱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

በትልልቅ ሰዎች ላይ ክትባቱ በትክክል የሚሰራ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ አዛውንቶች ቀጣዮቹ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል ማለት ነው። ወይም ደግሞ አዛውንቶችን የሚንከባከቡ ሰዎች ከእነርሱ ጋር ንክኪ ስለሚኖራቸው እነሱም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ወገኖች መካከል ናቸው።

የመድሃኒቱ ሁኔታስ?

ሐኪሞች የጸረ ቫይረስ መድሃኒት እየቀመሙ ሲሆን ይህም በኮሮናቫይረስ ላይ ይሰራ እንደሆን እየሞከሩ ነው። ይህም ሰዎችን ማዳን የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ምርምሮች በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰሩ ይገኛሉ።

ቫይረሱ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰባቸው አገራት ላይ በየካቲት ወር ሙከራው ተካሂዶ ነበር። ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ብሩስ አይልዋርድ "በአሁኑ ወቅት ውጤታማና በትክክል ይሰራል ብለን የምናስበው አንድ መድሃኒት ብቻ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም።

ይህም መድሃኒት ለኢቦላ ተብሎ የተዘጋጀ ሲሆን በርካታ የቫይረስ አይነቶችን እንደሚገድል ተረጋግጧል። ቢሆንም ግን በኮሮናቫይረስ ላይ የሚኖረው ፈዋሽነት የሙከራ ውጤቱ እየተጠበቀ ነው።

Image copyright Science Photo Library
አጭር የምስል መግለጫ የክትባት ናሙና

በሁለት የኤችአይቪ መድሃኒቶች (ሎፒናቪር እና ሪቶናቪር) ላይ ትልቅ ተስፋ ተጥሎ ነበር፤ የሙከራ ውጤቱ ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው የሆነው። ሰርቷል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።

መድሃኒቶቹ ምንም መሻሻል አላሳዩም፤ የኮቪድ-19 በሽታ የበረታባቸውን መፈወስም ሆነ ከሞት መታደግ አልቻለም። በጣም ከበረታባቸው ሰዎች ላይ ሲሞከር መድሃኒቱ ቫይረሱን መዋጋት የሚጀምረው በጣም ዘግይቶ ነው። ምናልባትም ሊሞቱ ሲቃረቡ ማለት ነው።

በእርግጥ የወባ በሽታ መድሃኒት (ክሎሮኩን) ላይም የመስራት ሰፊ ፍላጎት አለ። በቤተ ሙከራ በተደረገ ሙከራ መድሃኒቱ በትክክል እንደሚሰራ ቢረጋገጥም ታማሚዎች ላይ ግን ሙከራ ተደርጎ ውጤቱ ገና አልታወቀም። ሙከራዎች በአሜሪካና በሌሎች አገራት ላይም በመደረግ ላይ ናቸው።

ታዲያ ክትባት ወይም መድኒት እስኪገኝ ምን እናድርግ?

አሁን ላይ ያለው የተሻለውና ከኮሮናቫይረስ ሊከላከል የሚችለው ክትባት እጅን በደንብ መታጠብ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ በበሽታው ከተያዙ ደግሞ በሽታው ብዙ ሊባል በሚችል ሰው ላይ ስለማይበረታ በቀላሉ ቤትዎ ውስጥ አርፈው ፓራስታሞል እየወሰዱና በርካታ ፈሳሽ ነገሮችን እየተጠቀሙ ራስዎን ማስታመም ይችላሉ።

አንዳንድ ሰዎች ተጨማሪ በሽታዎች ሊኖሩባቸው ስለሚችል እነሱ ሆስፒታል ገብተው መታከም ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

ክትባቶች እንዴት ነው የሚሰሩት?

ክትባቶች ሰውነትን በማይጎዳ መልኩ በአካላችን ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው በሽታ ተከላካይ ሕዋሳቶቻችን ባክቴሪያዎችንና ቫይረሶችን እንዲያወቋቸው ያደርጋሉ። ከዚያም ሰውነታችን እውቅና ይኖረውና እነዚህ ቫይረሶች ወይም ባክቴሪያዎችን እንደ ወራሪ ስለሚያያቸው ባጋጠሙት ጊዜ ወዲያውኑ መዋጋት ይጀምራል።

ሰውነታችን ከዚያ በፊት ተጠቅቶ ቢሆን እንኳ እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ወዲያውኑ ሥራቸውን ይጀምራሉ።

የኩፍኝና የሌሎች ህመሞች ክትባቶች የተሰሩት በጣም የተዳከሙና ለበሽታ የማይዳረጉ ቫይረሶችን በመጠቀም ሲሆን በየወቅቱ ለሚቀሰቀስ ጉንፋን የሚሰጠው ክትባት ደግሞ አቅማቸውን እንዲያጡ የተደረጉ ቫይረሶችን በማካተት ነው።

ለአዲሱ የኮሮናቫይረስ የሚሰራው ግን አዲስ ነው፤ በትንሹ በመሞከር የሚሰራ ነው። "መሞከር እና ውጤቱን ማየት" አይነት የሙከራ አካሄድ ነው ሳይንቲስቶች የሚጠቀሙት። ምክንያቱም የአዲሱ ኮሮናቫይረስ ተፈጥሯዊ መዋቅር ስለሚታወቅ ቫይረሱን ለመስራት አስፈላጊው መረጃ ስላለ ነው።

አንዳንድ የክትባት ሳይንቲስቶች የተወሰነ የኮሮናቫይረስን የመራቢያ ኮድ ናሙና በመውሰድ ከሌላው ላይ ሲጨምሩት ቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ ምንም ጉዳት የማያመጣ ይሆናል።

ከዚህ በኋላ የሆነን ሰው በዚህ በተገኘው ውጤት እንዲያዝ ቢደረግ በጽንስ ሃሳብ ደረጃ ይህ ሰው የመከላከል አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።

ሌሎች ሳይንቲስቶች ደግሞ የዘረ መል ኮድ (ዲኤንኤ ወይም አርኤንኤ) ይወስዱና ወደ ሰውነት ይጨምሩታል። በዚህም የቫይረስ ፕሮቲን ማመንጨት በመጀመር የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ቫይረሱን እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው መማር ይጀምራሉ።