ኮሮናቫይረስ ባስከተለው የደም እጥረት በአማራ ክልል የቀጠሮ ቀዶ ህክምናዎች ተሰረዙ

ደም ለጋሽ Image copyright Getty Images

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የደም ለጋሾች ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት በቀጠሮ የሚደረጉ ቀዶ ህክምናዎች እንዲሰረዙ መደረጋቸውን የባህር ዳር ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ምክሩ ሽፈራው ለቢቢሲ ተናገሩ።

እንደ አቶ ምክሩ ገለጻ ከሆነ ለደም ባንኩ በሳምንት እስከ 400 ሰው ደም ይለግስ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት አምስት ሰዎች ብቻ ናቸው የለገሱት።

ደም የመጠቀሚያ ጊዜ እንዳለው ያስታወቁት ኃላፊው አንድ የደም ባንክ የደም ክምችት የሚኖረው 20 ቀን ነው ብለዋል።

በዚህ ምክንያት አሁን ባንኩ እስከ መጋቢት 20 ደረስ ብቻ የሚያገለግል ደም እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በቀጠሮ የሚደረግ ቀዶ ህክምና እንዲሰረዝ እና ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ግዜ እንዲቀጠሩ ተደረገዋል።

"ለወላድ፣ ለህጻናት እና ለመኪና እና ድንገተኛ አደጋ ለኩላሊት እና ለካንሰር በሽተኞች ግዴታ ስለሆነ እና ማራዘም ስለማንችል ብቻ ለእነሱ እንሰጣለን" ብለዋል።

ተኝተው ለሚታከሙም ቢሆን ካለው ችግር አንጻር ቀይ የደም ሴል እጥረት ላለባቸው ደም እንደማይቀርብ አሳውቀዋል።

የደም ልገሳው መቀዛቀዝ እንዴት ከኮሮናቫይረስ ጋር መመያያዙን አወቃችሁ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ በወር እስከ ሁለት ሺህ ደም ሰብስበው እንደሚያውቁ የገለጹት ኃላፊው፤ የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰት መገለጹን ተከትሎ መቀዛቀዙን ጠቁመዋል።

አብዛኛው ጊዜ የደም ልገሳ የሚካሄደው በትምህርት ቤቶች፣ ስብስባዎች፣ ፋብሪካዎች አና ሌሎችም ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች ነበር።

ሆኖም ኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከተነገረ በኋላ ትምህር ቤቶች በመዘጋታቸው እና ህዝብ የሚሰበሰብባቸው መድረኮች መሰረዛቸው የደም ማሰባሰብ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል።

የደም ባንኩ ዝቅ ያለውን የህብረተሰቡን የደም ልገሳ ለማሳደግ በባህር ዳር ከተማ ከማስተዋወቅ ባለፈ ከሰኞ ጀምሮ በጊዜያዊ ጣቢያዎች ደም በማሰባበሰብ ላይ ይገኛል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ቀናት 20 ዩኒት ደም መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻም የደም ልገሳ ፕሮግራም ይካሄዳል።

የባህር ዳር የደም ባንክ በሳምንት ከ400 ሰው የተለገሰውን ከተላላፊ በስታዎች ነጻ አድርጎ እስከ 25 ለሚደርሱ ሆስፒታሎች ያሰራጭ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች