ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ ግዛቶችን ዳግም ወደ ስራ ለመመለስ የሚረዳ እቅድ አስተዋወቁ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአሜሪካ እየተስፋፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለተለያዩ ግዛት አስተዳዳሪዎች በሚቀጥሉት ወራት ግዛቶቻቸውን ወደ ሥራ መመለስ የሚያስችል መመሪያ ሰጡ።

መመሪያው "አሜሪካን ዳግም ወደ ስራ መመለስ" የሚል ሲሆን ባለ ሦስት ምዕራፍ ነው ተብሏል።

ይህም ግዛቶች ቀስ በቀስ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ትዕዛዛቸውን እንዲያላሉ ያስችላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለግዛቶቹ አስተዳዳሪዎቹ ከተሞቻቸውን ለእንቅስቃሴ የመክፈቱን ሂደቱን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በጋራ በመሆን ራሳቸው እንደሚያከናውኑት ቃል ገብተዋል።

አሜሪካ እስካሁን ድረስ 654,301 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 32,186 መሞታቸው ታውቋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አንዳንድ ከተሞች በዚህ ወር እንዲከፈቱ ሃሳብ አቅርበዋል።

ትራምፕ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ምን አሉ?

ትራምፕ ትናንት ምሽት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ "በጦርነታችን ላይ ቀጣዩ ምዕራፍ አሜሪካን ዳግም ወደ ስራ መመለስ ነው" ብለው ነበር።

"አሜሪካና አሜሪካውያን ዳግም ወደ ስራ መመለስ ይፈልጋሉ" በማለትም " አጠቃላይ አገሪቱን ከእንቅስቃሴ ውጪ ማድረግ የረዥም ጊዜ መፍትሄና አዋጭ አይደለም" ብለዋል።

አክለውም ለረዥም ጊዜ ሰዎች በቤት እንዲቀመጡ ማድረግ አደገኛ የሆነ የማህበረሰብ ጤና ቀውስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚዎች፣ የጠጪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራሉ፣ የልብ እና የ" አካላዊና የአእምሮ" ጤና ችግሮችም ይስተዋላሉ ብለዋል።

ትራምፕ ጤናማ ዜጎች "ሁኔታዎች ከፈቀዱ" ወደ ስራ መመለስ ይፈልጋሉ ያሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም አሜሪካውያን አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ ጤንነት ካልተሰማቸው ደግሞ ቤታቸው እንዲቀመጡ ይመከራል ብለዋል።

የአሜሪካን ኢኮኖሚ ዳግም ወደ ስራ ለመመለስ "ጥንቃቄ የተሞላበት አንድ እርምጃ በአንድ ጊዜ" ይወሰዳል ካሉ በኋላ የግዛቶቹን አስተዳዳሪዎች ግን "ማድረግ የሚፈልጉትን በጣም በጣም በፍጥነት" እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

የዲሞክራቶች መሪ የሆኑት ናንሲ ፒሎሲ ግን እቅዱን " አሻሚና ወጥነት የሌለው" ሲሉ አጣጥለውት ነበር።

የትራምፕ እቅድ ምንድን ነው?

ትራምፕ በዚህ በባለ 18 ገጽ ሰነድ ግዛቶች ዳግም እንዴት ወደ እንቅስቃሴ እንደሚመለሱ አስቀምጠዋል። በዚህ እቅድ መሰረት እያንዳንዱ ምዕራፍ በትንሹ 14 ቀናት ተሰፍረውለታል።

በእያንዳንዱ ምዕራፍ ጥሩ የንጽህና አጠባበቅ እና ቀጣሪዎች በሰራተኞቻቸው መካከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ መፈፀሙን እንዲያረጋጡ፣ ምርመራ እና ንክኪዎችን መለየትን መከናወኑን እንዲያረጋገጡ ይጠይቃል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ አሁን ባለው የእንቅስቃሴ ገደብ አላስፈላጊ የተባሉ ጉዞዎች፣ በቡድን መሰባሰብ እንደተከለከሉ ናቸው። ነገር ግን ምግብ ቤቶች፣ የአምልኮ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች "ጥብቅ የሆነ የአካላዊ ርቀትን መጠበቅ ተግባራዊ ተደርጎ መስራት ይችላሉ" ተብሏል።

በዚህ ወቅት የኮሮናቫይረስ መዛመት የማይታይ ከሆነ ወደ ምዕራፍ ሁለት የሚገባ ሲሆን በዚህም ወቅት አላስፈላጊ የተባሉ ጉዞዎች ተፈቅደዋል። በዚህ ወቅት ትምህርት ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።

ይህ ግን የሚሆነው የሚይዙት ሰው ቁጥር ተቀንሶ መሆኑ ተቀምጧል።

በሶስተኛው ምዕራፍ ዝቅተኛ የሆነ የቫይረሱ ስርጭት የሚታይባቸው ግዛቶች "የህዝብ ቅርርብን" ሊፈቅዱ ይችላሉ።

ይህ ግን የሚሆነው አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዳለ ሆኖ ነው ተብሏል።

በዚህ ወቅት ሆስፒታልና የአዛውንቶች መንከባከቢያ ስፍራን መጎብኘት ይፈቀዳል፤ መጠጥ ቤቶችም የሚያስተናግዷቸውን ሰዎች ቁጥር ከፍ ያደርጋሉ።

በዚህ ምዕራፍ አንዳንድ ግዛቶች ወደመደበኛ ህይወታቸው ተጠቃለው ሊገቡ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ይህ ሁሉ ግን በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ባሉባቸውና ቫይረሱ ዳግም በሚያገረሽባቸው ግዛቶች ረዘም ያለ ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል በእቅዱ ላይ ተቀምጧል።

ይህ ሦስተኛው ምዕራፍ "አዲሱ የህይወት ዘዬ" ነው የተባለ ሲሆን፣ ነገር ግን ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ህዝብ ከሚሰበሰበበ ስፍራዎች መራቅ አለባቸው ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግዛቶች ወደ ቀደመው ህይወታቸው እንዲመለሱና ኢኮኖሚው መንቀሳቀስ እንዲጀምር ይወትውቱ እንጂ የኒው ዮርኩ ገዢ አንድሪው ኩሞ ለቀጣዮቹ አንድ ወር ኒው ዮርካውያን ከቤት ሳይወጡ ይቆያሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በኒው ዮርክ በዚህ ሳምንት የቫይረሱ ስርጭት መረጋጋት ያሳያል የተባለ ሲሆን አሁንም ግን የሟቾቹ ቁጥር እየጨመረ ነው።

የሚቺጋን፣ የኦሃዮ፣ የዊስኮንሲን፣ የሚኒሶታ፣ የኢሊኖይስ፣ የኢንዲያና እና የኬንታኪ አስተዳዳሪዎች ክልሎቻቸውን ወደ ስራ ለማስገባት በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

እነዚህ አስተዳዳሪዎች ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ባይኖርም የተለያዩ የምጣኔ ሃነብት ዘርፎችም በምዕራፍ ምዕራፍ ከፋፍሎ ለማስጀመር ማቀዳቸው ታውቋል።

በሚችጋን 1,700 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት የሞቱ ሲሆን አስተዳዳሪው ግሪቸን ዊትሜር በወሰዱት የቤት መቀመጥ እርምጃ ነዋሪዎች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።