ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ግርፋት እንዲቆም ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዘዘ

ግርፋት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳኡዲ አረቢያ ግርፋትን መቀጣጫ ማድረግ ልታቆም እንደሆነ አንድ ለመገናኛ ብዙሃን የተላከ ሕጋዊ ሰነድ ጠቆመ።

ከሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ያጠፉ ሰዎች ከግርፋት ይልቅ በእሥራት ወይም በገንዘብ እንዲቀጡ ይደረጋል።

ሰነዱ፤ ይህ የንጉሥ ሰልማንና ልጃቸው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐማድ ቢን ሰልማን የሰብዓዊ መብት ለውጥ እርምጃ አካል ነው ይላል።

ሳኡዲ መንግሥትን የተቃወሙ ሰዎችን በማሠርና በጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ግድያ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትችት ሲደርስባት ቆይቷል።

የሳኡዲ እርምጃዎች የሚቃወሙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ ሃገሪቱ ሰብዓዊ መብት በመርገጥ ወደር የላትም ሲሉ ይወነጅላሉ። ሐሳብን በነፃነት መግለፅ በእጅጉ የታፈነ ነው፤ መንግሥትን መቃመው ደግሞ ለምክንያት የለሽ እሥር ይዳርጋል ይላሉ።

መጥፎ ገፅታ

በግሪጎሪ አቆጣጠር 2015 ላይ ሳኡዲ አራቢያዊው ጦማሪ ራይፍ ባዳዊ በአደባባይ መገረፉ አይዘነጋም። 'የሳይበር' ወንጀል ፈፅሟል፤ እስልምናን አንቋሿል ተብሎ ነበር የተቀጣው።

የምስሉ መግለጫ,

ሳዑዲ አራቢያዊው ጦማሪ ራይፍ ባዳዊ በአደባባይ መገረፉ አይዘነጋም

ጦማሪው በየሳምንቱ አንድ አንድ ሺህ ልምጭ እንዲገረፍ ነበር የተወሰነበት። ነገር ግን ግለሰቡ በግርፋሩ ምክንያት ሊሞት ደርሶ ነበር መባሉን ተከትሎ ተቃውሞ የበረታባት ሳኡዲ ግርፋቱ እንዲቆም አዘዘች።

ተንታኞች ግርፋት ለሳኡዲ መጥፎ ገፅታ እየሰጣት ስለሆነ ነው ለማቆም የወሰነችው ይላሉ።

ቢሆንም ንጉሡንም ሆነ አልጋ ወራሹን የሚቃወሙ ሰዎች አሁንም እየታሠሩ እንደሆነ ይዘገባል።

ባለፈው አርብ ሳኡዲ ውስጥ ስለሰብዓዊ መብት በመከራከር የሚታወቅ አንድ ግለሰብ እሥር ቤት ውስጥ ያለ በስትሮክ መሞቱ ተነግሯል። የሙያ አጋሮቹ የሕክምና እርዳታ ቢያገኝ ኖሮ ይድን ነበር ይላሉ።