የኮሮናቫይረስ ስጋት በሆነበት ወቅት ቤቶችን ማፍረስ "ኢሰብአዊነት" ነው በማለት አምነስቲ ኮነነ

ለገጣፎ/ለገዳዲ የፈረሱ ቤቶች
የምስሉ መግለጫ,

ፎቶው ለገጣፎ/ለገዳዲ የፈረሱ ቤቶችን የሚያሳይ ሲሆን በየካቲት ወር ላይ የፈረሱ ናቸው

የአዲስ አበባ አስተዳደር ህጋዊ ይዞታ የላቸውም በማለት በርካታ ቤቶችን ማፍረሱ እንዲሁም ቤተሰቦች መፈናቀላቸውን አምነስቲ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ኮንኗል።

በባለፉት ሶስት ሳምንታት በአብዛኛው በግንባታ ስራ የተሰማሩ የቀን ሰራተኞች ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶች በመፍረሳቸው ቢያንስ አንድ ሺ የሚሆኑ ሰዎችን ቤት አልባ ማድረጉን የገለፀው መግለጫው በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መሆኑ ደግሞ ነገሩን የከፋ አድርጎታል ብሏል።

ብዙዎቹ ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ጫና ስራቸውን ያጡ ግለሰቦች መሆናቸውን ያስታወሰው የአምነስቲ መግለጫ ባለስልጣናቱ በዚህ ሳይገቱ ለማደሪያ እንዲሁም ራሳቸውን ከዝናብ ለመከላለከል ብለው የሰሯቸውንም የፕላስቲክ እንዲሁም ጊዜያዊ መጠለያዎች በማፍረስ እንቅልፍ እያሳጧቸውም ነው ብሏል።

"ቤታቸው የፈረሰባቸውና መሄጃ ያጡ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ሜዳ ላይ ዝናብ እየወረደባቸው በብርድ ውጭ እንደሚያድሩ በአሳዛኘኝ ሁኔታ ነግረውናል" ያሉት በምስራቅና በደቡብ አፍሪካ የአምነስቲ ዳይሬክተር ዴፕሮዜ ሙቼና ናቸው

አክለውም "የኮቪድ-19 ስጋት በሆነበት ወቅት ቤት መኖር ራስን ለመጠበቅና ለማገገምም ወሳኝ ሁኔታ ነው። ባለስልጣናቱ ይህንን ተገንዝበው የኮሮናቫይረስ ስጋት በሆነበት ወቅት የሰዎችን ተጋላጭነት በመጨመር ቤት አልባ ሊያደርጓቸው አይገባም" ብለዋል።

በቦሌ ክፍለከተማ የሚገኙ ባለስልጣናት የካቲት መጨረሻ ላይ የተጀመረው ቤት ማፍረስ ህጋዊ ይዞታ የሌላቸው ላይ ያተኮረ መሆኑን ቢናገሩም አምነስቲ በበኩሉ ያናገራቸው ቤት የፈረሰባቸው ግለሰቦች በበኩላቸው ቦታቸውን ከአስራሶስት አመታት በፊት ከአርሶ አደሮች በመግዛት ቤታቸውን እንደገነቡ ነው።

ባለስልጣናቱ በበኩላቸው የቦታዎቹን ግዥ ህጋዊነት እንደማያውቁና ቤተሰቦቹም የያዟቸው የጨረቃ ቤቶች መሆናቸውን አረጋግጠው የመሬቱን ግዢ የሚመለከተው በቀጥታ የአዲስ አበባ አስተዳደር መሆኑንም አሳውቀዋልል።

ሆኖም መጋቢት ወር ላይ ቤት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀምና ፕላስቲኮችን በመወጠር ድንኳን በመስራት ጊዜያዊ መጠለያ ቢሰሩም ባለስልጣናቱ ቁሳቁሶቻቸውን በመውሰድ እንዲሁም መጠለያዎቻቸውም እንዳፈረሱባቸውም መግለጫው አመላክቷል።

ቤት የማፍረሱ ሁኔታ በቀጣይነት የቀጠለ መሆኑንም ያስታወሰው መግለጫው ሚያዝያ 6፣ 2012ዓ.ም ሌላ ዙር የማፍረስ ሂደት እንደጀመረ አትቷል።

"በአዲስ አበባ ውስጥ በተከታታይነት እየተደረገ ያለው የቤት ማፍረስ ሁኔታ አሰቃቂ ኢሰብአዊነትን የሚያሳይ ነው። ህዝብ በኮሮናቫይረስ ስጋት ተሰቅዞ በተያዘበት ወቅት፣ ስራ አጥነት በተደራረበት ወቅት እንዲህ አይነት ተግባር መፈፀሙ አሳዛኝ ነው። ቀጣዩ ምግባቸው መቼ እንደሆነ የማያውቁ ሰዎችን ቤት አልባ በማድረግ ባለስልጣናቱ ሁኔታውን ወደከፋ ሁኔታ እየወሰዱት ነው።" በማለት ዴፕሮዜ ኮንነውታል።

አምነስቲ የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ማረጋገጥ ችያለሁ እንዳለው ከመጋቢት 28፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ አርባ በቅርብ የተሰሩ ቤቶች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ወይም መፍረሳቸውን ነው።

በአካባቢው ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊትና በኋላ የነበረውንም ምስል አነፃፅሯል፣ በቤቶቹም ፈንታ የተተከሉ ድንኳኖችም እንዳሉ በመግለጫው ውስጥ በተካተቱ ፎቶዎች አሳይቷል።

በአብዛኛው ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ የቀን ሰራተኞች ሲሆኑ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም ጋር ተያይዞ ግንባታዎች በመቆማቸው ከስራ ውጭም እንደሆኑ መግለጫው አትቷል።

አምነስቲ አናገርኳቸው ያላቸው ቤተሰቦች ያለምንም ማስጠንቂያ ቤቶቻቸው እንደፈረሱባቸውና፣ ባለስልጣናቱም መጥተው ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት አላማካሄዳቸውን አስረድተዋል። አምነስቲ በበኩሉ አለም አቀፉን ህግ በመጥቀስ ሰዎች ቤቶቹ የራሳቸው ይሁን፣ ኪራይ ወይም የያዙት ቦታ ቢሆን ከመፈናቀላቸው በፊት ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁ መመሪያዎች መተግበር ነበረባቸው ይላል።

አንዲት እናት ለአምነስቲ እንደተናገረችው መጋቢት 28፣2012 ዓ.ም ቤቷ ሲፈርስ በስራ ላይ የነበረች ሲሆን ጎረቤትም ደውሎ እንደነገራት ገልፃለች።

"ቤቴ ከፈረሰ በኋላ አራት ልጆቼንም ሆነ ራሴን ከዝናብ ለመጠለል በፕላስቲክ ተጠቅልለን ነው የምንተኛው። ተቀያሪ ቤትም መስራት ኦልቻልንም ምክንያቱም ፖሊስ ድንኳናችን እየወሰደብን ስለሆነ" ብላለች

ስሟ እንዳይገለፅ የጠየቀችው ይህች ግለሰብ የአካባቢው ባለስልጣናት ስለመፈናቀላቸውም ሆነ ለሚዲያ የተናገሩትን እያሰረ ነው ማለቷንም አምነስቲ በመግለጫው አካቷል።

"ባለስልጣናቱ ከየቤታቸው የሚያፈናቅሏቸውን እንዲያቆሙ፤ ቤታቸውም ለፈረሰባቸው ተተኪ ቤቶች መሰጣታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ለወደፊቱም ጉዳቱ ከደረሰባቸው ቤተሰቦች ጋር ውይይት እንዲደረግና ችግሩን ከስር መሰረቱ መቀረፍ አለበት። "በማለት ዴፕሮዜ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።