ኮሮናቫይረስ፡ የቻይናና የአፍሪካ ግንኙነት በኮሮና ዘመን ምን ድረስ ይዘልቃል?

ቻይና ለአፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ለአፍሪካ አገራት ዋነኛ አበዳሪና የንግድ አጋር ስትሆን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ምንም እንኳ በእዳ ስረዛም ሆነ ቅነሳ ላይ ምንም ማለት ባትፈልግም በዲፕሎማሲ ረገድ ግን ግንኙነቷን አጠናክራለች።

ኮቪድ-19 በአፍሪካ ከተስፋፋ በኋላ ቤዢንግ የሰብዓዊ እርዳታ እጇን ለአፍሪካ አገራት ዘርግታለች።

በዚህ ሁሉ ግን የአፍሪካ አገራት የእዳ መክፈያ ጊዜያቸው ለተወሰነ ፋታ እንዲያገኙ፣ እንዲሰረዛላቸው አልያም እንዲቀነስላቸው ቢጠይቁም ቻይና "ጆሮ ዳባ" ብላለች።

በቻይና የሚገኙ አፍሪካውያን ቫይረሱን ያስፋፋሉ በሚል ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው የተሰማው ደግሞ በፈረንጆቹ የሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ ሲሆን ቤይዢንግ ግን ጉዳዩን አስተባብላለች።

ይህ በርካታ አፍሪካውያን የቻይና አፍሪካ ግንኙነት ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ የአፍሪካ መገናኛ ብዙኀን አገሪቱ የቫይረሱን ወረርሽኝ የያዘችበትን መንገድ ሲያንቆለጳጵሱ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቻይናን ከዘረኝነት ጋር አያይዘው በማንሳት የራሷን ጥቅም ብቻ የምታስቀድም አድርጎ መሳል እየተስተዋለ ነው።

ባለፉት አስርታት ቻይና የአፍሪካ ሁነኛ አበዳሪ ሆናለች። ከምዕራባውያን በተለየ ለአፍሪካ መሪዎች ያለምንም የአስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ብድርና እርዳታ መስጠት የቻይና መለያ ባህሪዋ ነው።

በምላሹም ቻይና በአፍሪካ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የመሰማራት እድል አግኝታለች።

የሕክምና ዲፕሎማሲ

እአአ ማርች 10 የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቤይዢንግ ለአፍሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ስራ ገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናገረ።

የገንዘቡ አሰጣጡ ዝርዝር ያልተገለፀ ሲሆን በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የኮቪድ-19 መመርመሪያዎችና የመከላከያ መሳሪያዎች በአሊባባ መስራች በቻይናዊው ቢሊየነር ጃክ ማ በኩል ለአፍሪካ ተሰጥቷል።

በዚህ ሳምንት ቢሊየነሩ ጃክ ማ ሶስተኛውን ዙር እርዳታውን ለ54 የአፍሪካ አገራት መስጠቱ ተሰምቷል።

ይህ የቅርብ ጊዜ እርዳታ ብቻ 4.6 ሚሊየን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ 500,000 የመመርመሪያ መሳሪያዎች፣ 300 ቬንትሌተሮች እና 200 ሺህ ለሕክምና ባለሙያዎች የሚያገለግሉ የመከላከያ አልባሳት ተካትቶባቸዋል።

ኮቪድ-19 ቻይና በአፍሪካ ላይ ያላትን ተጽዕኖ እንድታገዝፍ ከምዕራባውያን፣ በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት እንዲቀዛቀዝ ለማድረግ እድል ሰጥቷታል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ በርካታ የአፍሪካ መዎችን በማነጋገር እርዳታ ለመስጠት ቃል በመግባት አጋርነታቸውን ገልፀዋል።

የአገሪቱ የዜናተቋም ዢንዋ በየዕለቱ በአፍሪካ አገራት የሚገኙ ኢምባሲዎች ለአገራቱ እርዳታ ሲሰጡ የሚያሳይ ዘገባ ይዞ ይወጣል።

በሩዋንዳ የቻይና አምባሳደር "አለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመመከት የቻይናን ጥበብና ጥንካሬ" ለማስተዋወቅ ቃል ሲገቡ ተደምጧል።

ይህ የቻይና ዘመቻ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ በአገሪቱ ሚዲያና በከበርቴ የንግድ ሰዎቿ በኩል የሚካሄድ ነው።

እነዚህ ከፍተኛ የሆነ የመገናኛ ብዙኀን ሽፋን ያገኙ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፎች ቻይናን ብቁ፣ አስተማማኝ አጋር መሆኗን በአህጉሪቱ መሪዎችና ሕዝቦች ፊት አድርጎ ለመሳል ያለሙ ናቸው።

እነዚህ የሕክምና ቁሳቁስ እርዳታዎች ምንም ትንሽ ቢሆኑም በቻይና መገናኛ ብዙኀን ሲጂቲኤን (የቻይና ዓለም አቀፍ የቲቪ ኔትወርክ) እና የአገሪቱ የዜና ኤጀንሲ፣ ዢንዋ ከፍተኛ ሽፋን የሚያገኙ ይሆናል።

የመገናኛ ብዙኀኑ ዘገባዎች የሚያጠነጥኑት ቻይና የአፍሪካን ችግር ለመካፈል፣ ሕዝቦቿም ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ " አስተማማኝ አጋር"ና "አጋርነት" የሚል ቃል ይጠቀማሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ መገናኛ ብዙኀን ምን አሉ?

የናይጄሪያ ጋዜጣ "ዘ ፐንች" በፈረንጆቹ የሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ቻይናውያን ዶክተሮች ናይጄሪያ መግባታቸውን ተከትሎ ትችት አዘል ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

ከሁለት ቀን ቀደም ብሎም ራዲዮ ቢያፍራ ናይጄሪያ ቻይና ጥቅሟን ብቻ ፈላጊ አንደሆነች አድርጎ በመሳል የሕክምና ቁሳቁሶችን እንዳትቀበል የሚጠይቅ ዘገባ አስተላልፏል።

ይህ ትችት ደግሞ እየበረታ የመጣው በጉዋንዡ የሚገኙ አፍሪካውያን ከሚኖሩበት አፓርትመንት እና ሆቴሎች እንዲወጡ ሲደረጉና ኮሮናቫይረስን ታስፋፋላችሁ በሚል ወደ ለይቶ ማቆያ ሲገቡ የሚያሳይ ምስል ከታየ በኋላ ነው።

ይህ መረጃ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ሲዘዋወር የነበረ ሲሆን በቻይና የሚገኙ የአንዳንድ አፍሪካ አገራት ዲፕሎማቶችም ለአገሪቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የኬንያው ጋዜጣ ዴይሊ ኔሽን በበኩሉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ቻይና መሆኗ እየታወቀ አፍሪካውያንንን ቫይረሱን ታሰራጫላችሁ በሚል ማንገላታት "ነውር" መሆኑን የሚያትት ዘገባ ይዞ ወጥቷል።

ሌላው የኬኒያ ጋዜጣ ዘ ስታንደርድ፣ ቻይና በአፍሪካውያን ላይ የምታደርሰውን ዘረኝነት የተሞላበት ተግባር ከኮነነ በኋላ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ቻይናውያን እጣ እንደሚያሰጋው አትቷል።

የደቡብ አፍሪካ ዴይሊ ማቭሪክ ድረገፅ በበኩሉ አፍሪካውያን በቻይና የሚደርስባቸው ዘረኝነት የተሞላበት ጥቃት "ከላይ ከላይ ሲታይ ውጤታማ የሚመስለውን የቻይናና አፍሪካ ግንኙነት አደጋ ላይ ይጥለዋል" ብሏል።

ይህ ለቻይና ያለው አሉታዊ አመለካከት በትዊተርና ፌስቡክ ተጠቃሚ አፍሪካውያንም ዘንድ ተስተውሏል።

በእዳ ስረዛ ላይ ያለ ዝምታ

የቻይና ባለስልጣናት እና መገናኛ ብዙኀን በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ለአፍሪካ አገራት እንዲደረግ የተጠየቀውን የእዳ ስረዛ ጥያቄ እንዳላየ እንዳልሰማ አልፈውታል።

ቻይና በአፍሪካ ለሚካሄዱ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ብድር ታቀርባለች።

በዚህ በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምለ25 ደሃ አገራት 500 ሚሊየን ዶላር የእዳ ስረዛ ያደረገ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 19 የአፍሪካ አገራት ናቸው።

ቻይና ደግሞ በምላሹ ጉዳዩን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን እንደምታጤነው ተናግራለች።

ከዚህ ቀደም ብሎ የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር " የአፍሪካ እዳ አዘቅት ውስብስብ ነው እንዲሁም እያንዳንዱ ያለበት እዳ ይለያል" ብሎ ነበር።

አፍሪካ ሪፖርት የተሰኘው ድረ ገፅ " ቻይና አፍሪካ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስና የምጣኔ ሃብት ድቀት ለመታደግ አጥብቃ የምትፈልገውን የ145 ሚሊየን ዶላር እዳ ስረዛ ትሰጣታለች" የሚለው አይታወቅም ብሏል።

አፍሪካ በአሁኑ ሰአት አጥብቃ ለምትፈልገው የእዳ ስረዛ ቻይና የምትሰጠው ምላሽ የአህጉሪቱ አገራት ጋር ወደፊት የሚኖራትን ግንኙነት ይወስነው ይሆናል፤ ይህ ደግሞ የቫይረሱ ወረርሽኝ ጋብ ብሎ የምጣኔ ሃብት ተግዳሮቱ ጎልቶ ሲታይ የበለጠ ለፈተና የሚቀርብ ይሆናል።