ኮሮናቫይረስ: አማራ ክልል ሠርግ ላይ በፈነዳ ቦንብ ህይወት ጠፋ

ቢቢሲ አማርኛ

በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅና እናውጋ ወረዳ እናርጅ ሲማ ቀበሌ ትላንትና ምሽት ሲካሄድ በነበረ የሠርግ ሥነስርዓት ላይ በቦንብ ፈንድቶ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ።

ህይወታቸው ካለፉት በተጨማሪ አራት ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አራቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የእናርጅና እናውጋ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጥሩ ሴት መንግስት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከሟቾቹ አንዱ የሆኑት እና ቦንቡን ይዘውት የነበሩት ግለሰብ የሠርገኞቹ ቤተሰብ ሲሆኑ በአጋጣሚ የደረሰ ጉዳት እንጂ ሆን ተብሎ አለመሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ጉዳት ደረሰባቸው ግሰቦች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ከአራት በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው እንደ ሠርግ ያሉ ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ መከለከሉን ኃላፊዋ አስታውሰው በወረዳው ሠርግ እንዳይደገስ ርብርብ እየተየተደረገ ነው ብለዋል።

“ግለሰቦች ተነግሯቸው አይደገስም አሾልከን ዳርን በሚሉበት ወቅት ነው እንግዲህ ጉዳት የደረሰው። [ሠርጉ ላይ] ብዙ ሰው አልነበረም። ቦንብ የያዘውና ህይወቱ የጠፋው ግለሰብም አማች ነው። ሰርጉ እንዲቆም ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ነው ይህንን ድርጊት ሲፈጽም ጉዳት የደረሰው”ብለዋል።

“ቀደም ሲል የግንዛቤ ስራ ሰርተናል እምቢተኛውን ደግሞ በህግ ፊት እያቀረብን ነው። ለዚህ ወረዳው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው። በርካታ ግለሰቦች አቅርበን ጠይቀን በርካታ ሠርግ አቋርጠናል። ብዙዎችንም ተጠያቂ አድርገናል። ለበሽታው ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል በሚል አዋጁን በመጣስ ሰርግ እና ተስካር ደግሰው ከ41 በላይ ክስ የተመሰረታቸው ሰዎች አሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ከጉዳቱ ጋር ተጠርጣሪ በተያያዘ በቁጥጥር ስር ስለመዋሉ መረጃ የለኝም ያሉት ወይዘሮ ጥሩሰው “ቦንቡም የያዘው ህይወቱ አልፏል። ይህንን [ሠርጉን] የፈጸመውም ተጠያቂ የማይሆንበት ምክንያት የለም” ብለዋል።

የእናርጅና እናውጋ ወረዳ ፖሊስ በበኩሉ መርማሪዎችን ወደቦታው በማሰማራት ስለጉዳይ እየመረመረ መሆኑን ነግሮናል።